ትናንት ምሽት እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት፤ ቢያንስ 50 ፍልስጤማውያን መሞታቸውን በሃማስ የሚመራዉ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታውቋል።
እስራኤል ጥቃቱን የፈጸምኩት ሃማስ በአሜሪካ አደራዳሪነት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣሱ ነዉ ብላለች፡፡
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ሃማስ በደቡባዊ ጋዛ አንድ የእስራኤል ወታደር ገድሏል፤ የሟች ታጋቾችን አስከሬን ለመመለስ የተደረሰዉን ውልም ጥሷል ሲሉ ከሰዋል።
ሃማስ በበኩሉ ከጥቃቱ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽ ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ቁርጠኛ መሆኑን አስታዉቋል፡፡
የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱን የሚያደናቅፈው ምንም ነገር የለም ቢሉም፤እስራኤል ግን ወታደሮቿ ላይ ጥቃት ሲሰነዘርባት ‹‹መመለስ አለባት››ሲሉ አክለዋል።
እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት በጋዛ ከተማ እና በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና የመኖሪያ ህንጻዎች ተመተዋል።
የሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ ፤ በጥቃቱ ቢያንስ 50 ሰዎች ሲሞቱ 22 ህጻናትን ጨምሮ ሌሎች 2መቶ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የሕይወት አድን ሠራተኞች ‹‹በተደጋጋሚ በሚፈጸመው የአየር ድብደባ መካከል እና በግብዓት እጥረት ውስጥ ሆነው በአስቸጋሪ ሁኔታ ሕይወት ለማትረፍ እየሰሩ ነው››ብለዋል።
ማክሰኞ ምሽት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሰጠው አጭር መግለጫ፤ የአገሪቱ ጦር ‹‹ከባድ ድብደባ››እንዲፈጽም መታዘዙን የገለፀ ሲሆን፤ ምክንያቶቹን ግን አላሳወቀም።
ካትዝ ግን ማክሰኞ ዕለት ሐማስ በጋዛ በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት በመክፈት ‹‹በደማቁ የተሰመረውን ቀይ መስመር››ጥሷል ብለዋል።
‹‹ሐማስ ወታደሮቹ ላይ ጥቃት በመፈጸሙ እንዲሁም የተሰዉ ታጋቾችን ለመመለስ የገባውን ስምምነት በመጣሱ በተደጋጋሚ ዋጋ ይከፍላል›› ሲሉም አስጠንቅቀዋል እንደ ቢቢሲ ዘገባ።
ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም
