ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በመጠቀም 530 ሺሕ ቶን አሳ ማምረት እንደምትችል በጥናት መረጋገጡን የግብርና ሚኒስቴር ለአሐዱ ገልጿል።
በግብርና ሚኒስቴር የአሳ ሀብት ልማት ዴስክ ኃላፊ ዶ/ር ፋሲል ዳዊት ከዚህ ቀደም የአሳ ሀብት ስትራቴጂክ እቅድ እንዳልነበረው አስታውሰው፤ “አሁን ግን በዘርፉ የአስር ዓመት ማስተር ፕላን ተዘጋጅቷል” ብለዋል።
በአሳ ግብርና በጥናት የተረጋገጠውን ውጤት በተግባር ማምጣት ይቻላል ያሉት ዶ/ር ፋሲል፤ በኢትዮጵያ ባሉ የውሃ ሀብቶች ውስጥ ከ200 በላይ የአሳ ዝርያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህም መካከል 45 የሚሆኑት ብርቅዬ የአሳ ዝርያዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
አክለውም ይህንን ሀብት ለመጠቀም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቅንጅት ለመስራት መታቀዱን ለአሐዱ ጠቁመዋል።
የሌማት ትሩፉት ከተጀመረ አንስቶ የአሳ ሀብት ልማት በሦስት እጥፍ መጨመሩን ያነሱት ኃላፊው፤ “ከ255 ሺሕ ቶን በላይ ምርት በዓመት ይገኛል” ብለዋል።
በተጨማሪም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሚገኘው ሰው ሰራሽ ሐይቅ በቀን ከ14 ሺሕ ቶን በላይ ምርት እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም “የሚመረቱ አሳዎች በአይነታቸው ተፈላጊ የሆኑና ለምጣኔ ሃብቱም ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ የሆነ ነው” ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም የሕንድ ውቅያኖስ ክልል የዓሣ ኃብትን የማልማት አቅምን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የኢጋድ ምክክር መድረክ ከነሐሴ 6 እስከ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል።
የኢጋድ አባል ሀገራት የበለጸገ የዓሳ ሀብት ያላቸው ቢሆንም የዘርፉ ምርታማነት በበቂ ሁኔታ አለመበልጸጉን የሚያሳዩ ናቸው የተባለ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ የሚመረተው የዓሳ መጠን ወደ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ ይህም ከ30-40 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
