ትናንት የአርቲስት ደበበ እሸቱ የቀብር ስርዓት በአመዛኙ የመንግሥት ሰዎች በተገኙበት ተከናውኗል ። እንደ አርቲስቱ ታላቅነት ፣ እንደ አንጋፋነቱ ፣ ለኪነጥበቡ እንዳበረከተው አስተዋጽዖ የሚጠበቀውን ያህል ሰው በሽኝቱ ላይ አልተገኘም ።
አጋጣሚ ሆኖ የዛሬ 13 ዓመት ልክ በትናንቱ ዕለት የአቶ መለስ ሕልፈት ( በእርግጥ ቀኑ አወዛጋቢ ነው ) የተነገረበት ነው ። ሁለቱን ሰዎች ጎን ለጎን ያመጣኋቸው የሁለቱን ሕልፈት አስመልክቶ ስለተነከሰቱ አፈንጋጮች ( በባሕልና በስነምግባር ) ለማለት ነው ።
አቶ መለስ የሞቱ ጊዜ ከዲያስፖራዎች ጥቂት ተቃዋሚዎች በሞንታርቦ ሙዚቃ ከፍተውና ባንዲራ ለብሰው አደባባይ ላይ ሲጨፍሩ አቶ መለስን በሚቃወሟቸውና በሚጠሏቸው ጭምር ተወግዘዋል ። ምክንያቱም ነውሩ ከኢትዮጵያዊ ስነምግባር ያፈነገጠ በመሆኑ ።
በወቅቱ እንደ አጠቃላይ ሀገሬው ፣ ይበልጥ ደግሞ ተጋሩው ሀዘን ተሰምቷቸዋል ። ስሜታቸው ተጎድቷል ። ጉዳዩን ከብሔር መገለል ጋር ያያያዙትም ነበሩ ። በወቅቱ በድርጊቱ ያላዘነና ክፉ ያልተሰማው ተጋሩ ነበረ ብዬ አላምንም ።
ከእነዚያ ሰዎች ጥቂት የማይባሉት የአርቲስት ደበበ እሸቱ ሕልፈት ከተሰማ ዕለት አንስቶ ከበሮ እየደለቁ ይገኛሉ ። አስከሬን ሲሰድቡና ሲያንጓጥጡ ነው ውለው ያደሩት ። ትናንት በአስከሬን ሽኝቱም ሆነ ስርዓተ ቀብሩ ላይ ብዙ ሕዝብ አለመገኘቱ አንድ የተቃውሞ መንገድ አድርጌ እወስደዋለሁ ።
የሰዉ ሁሉ መብት ነው ። ማንም ሊከሰው አይችልም ። ራሱ ጋሽ ደበበ በሕይወት እያለ ” ብልጽግናን ትደግፋለህ ” ሲባል ” ደግ አደረግሁ ። እኔ ብልጽግናን ሳይሆን ዶ/ር ዐቢይን ነው የደገፍኩት ። ለእሱ ደግሞ ደግ አደረግሁ ” ብሏል ። ምርጫ ነው ። በግሌ ” ሙት አይወቀስም ” ከሚሉት መሐል አይደለሁም ።
ሰው ሲሞት በሕይወት እያለ በሰራው መልካም ተግባር እንደምናመሰግነው ባልተገባ ስራው ብንወቅሰው ነውር አይመስለኝም ። ወይም ነው ብዬ አላምንም ። ሰው መልካምም ቢሰራ ፣ ቢከፋም ለሌላው ነው ። ለራሱ ምንም አይደለም ። ሰው የመልካምና የክፉ አርአያ ነው ።
ሰው ከሞተ በኋላ በስራው ሲወቀስ ወደፊት በትንሳኤ ሲነሳ እንዲያስተካክለው አይደለም ። ሌሎች የተባለውን አይተው ” ነግ በእኔ ” እንዲሉ ነው ። አስከሬንን መስደብና ማንጓጠጥ ግን በምንም መመዘኛ ኢ – ሞራላዊ ነው ። በዚያን ወቅትም ” አቶ መለስን ኢትዮጵያ ላይ ባላቸው አቋም በግሌ ተቀዋሚያቸው ነኝ ።
ሆኖም ግን አሁን በሀገር ባሕል መሰረት ግብዐተ መሬታቸው ሳይፈጸም አንወቅሳቸውም ” እያሉ በጨዋ ደንብ አስተያየት የሰጡ ብዙ ናቸው ። የአቶ መለስ ሕልፈት ጊዜ ጥቂት ዲያስፖራዎች ያደረጉት ዛሬም ድረስ በነውርነቱ ተመዝግቦ ተቀምጧል ። ይህ ከሆነ ደግሞ በደበበ እሸቱ ላይ የተደረገውም ስህተት ነው ።
መርጦ ልክ መሆን የለም መቸም ። የጋሽ ደበበን የቀደመ ሀሳብና ስራ ( ለምሳሌ ከብልጽግና ጎን መቆሙንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን መደገፉን ) መቃወም ችግር የለውም ። መጥላትም ጠዪው በዚህ ይጠቀም ከሆነ ችግር የለውም ። በጋሽ ደበበ ሽኝትና ቀብር ላይ የሚጠበቀውን ያህል ሰው በሽኝቱ ላይ አለመገኘቱን ” ለምን ? ” የሚል የለም ።
የየባለቤቱ መብት ነው ። መንግሥትም በራሱ መንገድ ዘመኑን በአርቲስትነት ያሳለፈውን ደበበን በባለስልጣን ማዕረግ አስቀብሮታል ። አስከሬንን መሳደብና ማንቋሸሽ ግን የ ” ማንኛችን በነውር እንበልጣለን ? ” እንጂ ሌላ ምን ይሆናል ?
ከቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
