ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም በጀት አመት ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ከላከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) ሰባት ነጥብ 17 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር አግኝታለች፣ በ2018 ዓ.ም በጀት አመት ስምንት ቢሊየን ዶላር ለማግኘት እየተሰራ ነው ሲሉ የዲያስፖራ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዋና ዳይሬክተሩ አምባሳደር ፍጹም አረጋ አስታወቁ።
መንግስት የበጀት አመቱን እቅድ ለማሳካት ያሰበው ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ገንዘብ ለመላክ የሚያስችሉ የተለያዩ መንገዶችን በማሻሻል እና ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲን በማጠናከር እንደሆነ አምባሳደሩ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ ይህንን ያስታወቁት ከንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት እና በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙ ዲፕሎማቶች ጋር በበይነ መረብ ባደረጉት ውይይት መሆኑን ከፕሬስ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
መንግስት የገንዘብ ዝውውሩን ለመጨመር እና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ማድረጉን አምባሳደሩ አብራርተዋል ብሏል፤ ከዲያስፖራው ጋር ያለው ግንኙነት መሻሻል እና የገንዘብ ዝውውር ሂደቶችን ማቀላጠፍ የገንዘብ ፍሰቱን ያሳድገዋል ማለታቸውንም አካቷል።
በ2017 ዓ.ም የበጀት አመት 7 ነጥብ 17 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዲያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ከላከው ገንዘብ የውጭ ምንዛሪ መሰብሰብ ቢቻልም፣ ከዚህ የበለጠ አቅም እንዳለው አምባሳደር ፍፁም አረጋ በውይይቱ ወቅት ማብራራታቸውም ተጠቁሟል።
አክለውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር ለዲያስፖራው ማበረታቻ ፓኬጆችን እና የተሻሻሉ አገልግሎቶችን በቅርቡ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል ማለታቸውን ዘገባው አስታውቋል።
