የኢትዮጵያ መንግሥት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጎርጎሮሳውያኑ 2025 እስከ 2030 የሚዘልቅ የ6.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አዲስ የልማት ትብብር ማዕቀፍ ተፈራርመዋል።
አዲሱ የትብብር ማዕቀፍ የአየር ንብረት ለውጥን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስን የመቋቋም አቅምን በማጠናከር፣ ዘላቂ የምግብ ሥርዓቶችን በመገንባትና በገጠራማ አካባቢዎች ኑሮን ለማሻሻል ያለመ መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
እንዲሁም ሴቶችን በማብቃት ላይ በማተኮር፣ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አማካኝነት የልማት ፕሮግራሞችን በማዘመን፣ እንዲሁም እንደ ሴቶች፣ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞች ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ የኢትዮጵያን አጣዳፊ ችግሮች ለመፍታት ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
ማዕቀፉን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር 6.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል የተባለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት1.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ ተሰብስቧል ተብሏል።
ይህም 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ክፍተት ያለው ሲሆን ይህን ክፍተት መሙላት የማዕቀፉን ዓላማዎች ለማሳካትና ተፅዕኖ ፈጣሪ ውጤቶችን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ተመላክቷል።
በስምምነቱ የፊርማ ሥነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ሰመረታ ሰዋሰው እና የተመድ የኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭን ጨምሮ በሀገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የተመድ ኤጀንሲዎች የተውጣጡ ተወካዮች ተገኝተዋል።
