በእሁዱ ስብሰባ ላይ ሩሲያ፣ቻይና እና ፓኪስታን በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ በተኩስ አቁም እንዲቋጭ ለጸጥታው ምክር ቤት ጠይቀዋል፡፡
ባለ15 ዓባላቱ ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ በጉዳዩ ላይ እንዲሰጥም አገራቱ ያሳሰቡ ሲሆን አሜሪካ ጣልቃ መግባቷ ውጥረቱን ያባብሰዋል በሚል ወቅሰዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን “ሁሉም ዓለም ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን ስለመቱ ሊያመሰግናቸው ይገባል”በሚል የትራምፕን እርምጃ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሞክረዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢራኑ አምባሳደር አሚር ሳኢድ ኢራቫኒ አሜሪካ ጭፍን ጥቃት ሰንዝራብናች በሚል ከሰዋል፡፡
ልክ ባልሆነ ምክንያት ኢራን ላይ ዋሽንግተን ድብደባ ፈጽማለች የሚል ክስም አቅርበዋል በስብሰባው ላይ ኢራቫኒ፡፡
የቻይናው አምባሳደር ፉ ኮንግ በዚሁ መድረክ ላይ”ቤይጂንግ በብርቱው ጥቃቱን ትቃወማለች” ያሉ ሲሆን ሩሲያም ተቃውሞዋን አሰምታለች።
የሩሲያው አምባሳደር ቫሲሊ ነቤንዝያ ዋሽንግተን የዲፕሎማሲ ፍላጎት እንደሌላት ይጠቁማልም ብለዋል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የአሜሪካ ጥቃት ያልተረጋጋውን መካከለኛው ምስራቅ ወደ ተጨማሪ ቀውስ ይወስደዋል በሚል አሳስበዋል።
ጉቴሬዝ ሌላ የውድመት አዙሪትን መቋጨት አለብን የሚል ጥሪም አቅርበዋል፡፡
