10ኛው ዓለምአቀፍ የሆርቲካልቸር የንግድ ትርዒት (ሆርቲፍሎራ ኤክስፖ 2026) ከመጋቢት 15 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ተገለጠ።
የፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ከኤች.ፒ.ፒ. ኤግዚቢሽን ወርልድዋይድ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት ይህ ታላቅ ሁነት በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ አካላትን በአንድ ጣሪያ ስር ያሰባስባል ተብሏል።
በንግድ ትርዒቱ ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከተውጣጡ ከ50 በላይ ሀገራት የሚመጡ ከ150 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚ ባለሀብቶች፣ አምራቾች፣ የዘርና የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች እንዲሁም የፋይናንስና የሎጅስቲክስ ተቋማት ይሳተፋሉ።
ይህ መድረክ ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን፣ በኢንዱስትሪው ዘላቂ ልማት፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና በዓለምአቀፍ የገበያ ትስስር ዙሪያ ጠቃሚ ምክክሮች የሚደረጉበት መሆኑ ተጠቁሟል።
የዘንድሮው ኤክስፖ ልዩ የሚያደርገው፣ የግብርና ሚኒስቴር የ10 ዓመቱን ብሔራዊ የሆርቲካልቸር ልማት ስትራቴጂ እና የ15 ዓመቱን የአቮካዶ ልማት መርሃግብር ይፋ ካደረገ በኋላ የሚካሄድ የመጀመሪያው ግዙፍ ዓለምአቀፍ ሁነት በመሆኑ ነው።
በቆይታውም በምግብ ደህንነት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም፣ በባህር ጭነትና በዘላቂ ፋይናንስ ዙሪያ ያተኮሩ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል።
