የዓባይ ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቅ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ጥበቃ የሚያደርግ የ “ባህር ፖሊስ” መደራጀቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ነው ያስታወቀው ።
በፌዴራል ፖሊስ የሠራዊት ግንባታ ዋና መምሪያ ስር የኢንስፔክሽንና ስታንዳርድ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር እስከዳር ብርሃን እንደገለጹት የዓባይ ግድብ ላይ የተፈጠረውን ረጅምና ስፋት ያለውን ሰው ሠራሽ ሀይቅ ለመጠበቅ እና በአካባቢው ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል የ“ባሕር ፖሊስ” ወይም “ኮስታል ፖሊስ ጋርድ” ተቋቁሟል ፡፡
የዓባይ ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቅ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የጥበቃ ሥራው የሚከናወነው በፌዴራል ፖሊስ ሲሆን ሰው ሠራሽ ሐይቁን ለመጠበቅ የሚያስችል የሎጀስቲክስ አቅምን የማጠናከር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል ።
በሪፎርም ሥራው የወንጀል መከላከል፣ አድማ በታኝ፣ ፈጥኖ ደራሽና ሌሎች አደረጃጀቶች ላይ በተደረገው ጥናት ድሮን፣ ጀልባ፣ ሂሊኮፕተርና ሌሎች ትጥቆችን ማሟላት ትኩረት ተሠጥቷል ያሉት ኮማንደሯ፤ በዚህ መሠረትም የባሕር ላይ ውንብድናን መከላከል የሚችል ኃይልን ከትጥቅ ጋር የማደራጀት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ አደረጃጀቱን ወደ ሥራ ለማስገባትም ብቁ የሰው ኃይል የመመልመል እና የማሠልጠን ሥራን ከኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ጋር በትብብር እንደሚሠራ ጠቁመው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈለገውን የሰው ኃይል በመመልመልና በማሠልጠን ወደ ሥራ ይገባል። ነገር ግን መቼ ወደ ሥራ እንደሚገባ ቁርጥ ጊዜው አልታወቀም ብለዋል።
ይህ “ኮስታል ፖሊስ ጋርድ” ወይም የ“ባሕር ፖሊስ” ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን የተደራጀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ለፈጣንና ወቅታዊ መረጃዎች የቴሌግራም ገፃች
tiktok.com/@cc
