“የቀጣይ አድማስ” የሚል መሪ ቃል ያለው ይህ የሦስት ዓመታት ስትራቴጂ ተቋሙን ከቀላል የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪነት ወደ ዘመናዊና ሁለገብ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ከፍ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
“Next Hotzone Beyond Digital” በሚል ጽንሰ ሀሳብ ላይ የተመሰረተው ይህ አዲስ ስትራቴጂ፥ የኢትዮጵያን የዲጂታል ለውጥ እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።
ስትራቴጂው በርካታ ሀገራዊ ዕቅዶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሲሆን በተለይም የመንግስትን የ10 ዓመት የልማት እቅድ እና የኢትዮጵያን የዲጂታል ስትራቴጂ ለማላቅ ያስችላል ብለዋል።
ይህ አዲስ ስትራቴጂ የኢንዱስትሪውን የእድገት ማማ ለማላቅ እና ከአህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ውስጥ በመግባት የገበያ አድማሱን ለማስፋት የሚያስችል መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ኢትዮ ቴሌኮም ከቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር ሌሎች መልከ ብዙ የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ልህቀት አስተዋጽኦ ያደርጋልም ነው ያሉት።
ይህ አዲስ ምዕራፍ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘመን የምትጓዝበትን መንገድ ይበልጥ የሚያበራ መሆኑንም ገልጸዋል።
