በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቱሪዝም ዘርፍ ላይ በተደረገ የኦዲት ግኝት፣ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሆቴሎች የግዴታ የእሳት አደጋ መከላከያ ደንቦችን ሳያሟሉ የኮከብ ደረጃ እንደተሰጣቸው ተገለጸ።
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ከተሰጣቸው ሆቴሎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የእሳት አደጋ መከላከያ መስፈርቶችን እንዳላሟሉ ተገልጿል።
በ2017 ዓ.ም የተካሄደ የኦዲት ግኝት እንደሚያሳየው፣ በደረጃ ምደባ ከተካተቱት 113 ሆቴሎች ውስጥ 71 ያህሉ ከነጭራሹ የእሳት አደጋ መከላከያ የምስክር ወረቀት የላቸውም፡፡
በተጨማሪም፣ ከዚህ ዉስጥ 10 የሚሆኑት ሆቴሎች ዓመታዊ የእሳት አደጋ መከላከያ የምስክር ወረቀት እድሳት ያላደረጉ ናቸው፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት መሠረት፣ በምዘና መመሪያው ውስጥ አስገዳጅ ተብለው የተቀመጡት የእሳት አደጋ መከላከያ መስፈርቶች ሳይሟሉ ደረጃ የመስጠት አሠራር እንዳለ አመልክቷል።
ይህም ከሆቴሎች የደረጃ ምደባ መመሪያ ጋር የሚቃረን ሲሆን፣ ኦዲቱ ይህ አሠራር መቆም እንዳለበት አሳስቧል። የቱሪዝም ሚኒስቴር አዲስ የተቋቋሙ ሆቴሎች ሥራ ከጀመሩ በአንድ ዓመት ውስጥ መመዘንና ደረጃ ሊሰጣቸው ቢገባም፣ ይህ ተግባር አለመከናወኑ በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
የደረጃ ምደባ ከተከናወነ በኋላ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ አለመደረጉና አንዳንድ ጊዜም እስከ ሁለት ዓመት የሚዘገይ መሆኑ ተገልጿል።
CapitalNews
