በሳዑዲ ቴሌኮም የሴልስ ከርየር እና ሆልሴል ምክትል ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ዚያድ ሃማድ ኤ. አልሃሶን እና የከርየር ሴልስ ዳይሬክተር ሚስተር ባንደር ኤ. አልኮዳይር የተመራ ልዑክ ከኢትዮ ቴሌኮም ማኔጅመንት አባላት ጋር ውይይት አካሄዷል፡፡
ውይይቱ በሁለቱ ኦፕሬተሮች መካከል ያለውን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል የተባለ ሲሆን ነባሩን የቢዝነስ ትብብር ለማሳደግ፣ አዳዲስ የዕድገት አማራጮችን ለመክፈት እና የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ውይይቱን የመሩት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በወቅቱ “ለጋራ ተጠቃሚነት ብዙ ልንተባበርባቸው እና አዳዲስ የዕድገት አማራጮችን ልንፈልግላቸው የምንችላቸው ዘርፎች አሉ” ያሉ ሲሆን፤ “እነዚህም የአገሮቹን ዲጂታል ሽግግር የሚያሳድጉ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማትን የሚያፋጥኑ ዕድሎች ናቸው” ብለዋል።
በውይይቱ ኢትዮ ቴሌኮም እና የሳዑዲ ቴሌኮም ኩባንያ ያላቸውን ሀብት እና የጋራ ትብብር ሆልሴልን እና ከርየርን ለማስፋፋት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል የተባለ ሲሆን በተለይም በፊንቴክ፣ በአለም አቀፍ ሀዋላ፣ በተለያዩ የዲጂታል መፍትሄዎች እና በርካታ የቢዝነስ ዘርፎች ላይ የአዳዲስ እድሎችን በር የሚከፍት ይሆናል ተብሏል፡፡
