የኢሳይያስ ቃለምልልስ የገለጣቸው እውነቶች!
የአፍሪቃ ቀንድ መልሕቅ ኾና የኖረችው ኢትዮጵያ፣ በዕድሜም ኾነ በቆዳ ብዙ እጥፍ ከእርሷ በሚያንሱ ሀገራት ተከብባ ከባሕር የመነጠሏ ምዕራፍ ያበቃ ዘንድ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኩል ወደ ተዋሥዖ መድረኩ ብቅ ያለው የባሕር ተደራሽነት ጥያቄ፣ አያሌ ውርክብ ፈጥሯል ፤ ብዙ አቧራም አጭሷል፡፡ ኢትዮጵያ ሶማሊላንድን የመጫወቻ ካርድ አድርጋ የጀመረችው ይኽ ቁማር ታዲያ፣ በኤርትራ እና ሶማሊያ ዘንድ የፈጠረው ስሜት፣ በኢትዮጵያ ዙርያ የገሐነም ቅጥር ማበጀትን ሥልት እስከማድረግ የተጓዘ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በግብጽ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መንግሥታት መካከል ከጥቂት ወራት በፊት ታይቶ የነበረው የሤራ ቅንፍም ለዚህ አብነት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡
ሁኔታዎች ግን በታሰበላቸው ጥንካሬ ከመጓዝ ይልቅ ያልታሰበ ዝለት እየታየባቸው የመጣ ይመሥላል፡፡ ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ‹‹አለብኝ›› የምትለውን ችግር ለመፍታት በቀጥታ መነጋገርን መርጫለሁ የሚለው አቋሟን ከማስታወቋ ጀምሮ፣ ኤርትራ ከሰሞኑን በፕሬዝዳንቷ ኢሳይያስ አፈወርቂ በኩል ‹‹ያ የሦስትዮሽ ጥምረት ፈጽሞ ጸረ ኢትዮጵያ አልነበረም›› በማለት ለማስተባበል እስከሔደችበት ርቀት ድረስ፣ አልፎም ሶማሊያ በግዛት አንድነት ሥም የደለቀችው አታሞ የገደል ማሚቶ ኾኖ እንኳንስ ሶማሊላንድን ‹‹ጁባላንድን›› ጭምር እስከወዲያኛው በማጣት ቋፍ ላይ የመሰየሟን እውነታ ለተመለከተ፣ ነገሮች ሁሉ ለኢትዮጵያ ሰርግና ምላሽ እየኾኑ ነው ሊያስብለው ይችላል፡፡
***
ከቀናት በፊት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከሀገራቸው ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ወደ ሦስት ሰዓት የተቃረበ ቆይታን ሲያደርጉ፣ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል ከጥቂት ወራት በፊት መንግሥታቸው ከሶማሊያ እና ግብጽ መንግሥታት ጋር የፈጠረው ወታደራዊ የሚመስል ጥምረት ጉዳይ አንዱ ነበር፡፡
ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ በአሥመራ የተፈረመው ያ የሦስትዮሽ ስምምነት፣ ሶማሊያ ሶማሊላንድን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበትን ውጥረት መሠረት አድርጋ፣ ግብጽም ዐባይን ማዕከል ያደረገውን ታሪካዊ ባላንጣነቷን ተጠቅማ፣ ኤርትራም እንዲሁ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኩል የኢትዮጵያን ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነት በተመለከተ የተነሣውን ጥያቄ ተከትሎ የተፈጠረባት ድንጋጤ መግፍኤ ኾኗት የተፈራረመችው መኾኑ ግልጽ ቢኾንም፣ እርሳቸው ግን ስምምነቱ ‹‹ጸረ ኢትዮጵያ›› ነው ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ፣ ‹‹ይኽ ውዥንብር ለመፍጠር ታልሞ የተነዛ የሀሰት መረጃ ነው›› በማለት ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይኽን ምላሽ በመሥጠት ጥያቄውን ለማጣጣል የሞከሩት፣ ነገሩን ዲፕሎማሲያዊ ቅብ ሊያላብሱት አልያም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበትን ቀዝቃዛ ውጥረት ለማለዘብ አይመስልም፡፡ ከዚያ ይልቅ ያ የሦስትዮሽ ስምምነት ጸረ ኢትዮጵያ ሊኾን የማይችልበት ሁነኛ ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ‹‹እንኳን ዘንቦባት ቀድሞም ጤዛ ናት›› በሚለው ሀገርኛ ብሂል የተቋጠረ በመኾኑ ይመሥላል፡፡ ይኽንንም ፕሬዝደንቱ ‹‹ኢትዮጵያ ለራሷ በጣም አሳሳቢ ችግሮች ተጋርጠውባታል ፤ እናም በተቻለን አቅም ይህንን የገባችበትን ችግር ለመፍታት ከመሥራት ይልቅ ተጨማሪ ተግዳሮቶችን ልንፈጥርባት አንችልም›› በማለት፣ ሀገሪቱ ምንም ዐይነት ተጨማሪ ግፊት ሳያስፈልጋት ‹‹ራሷን እያፈረሰች ነው›› የሚል ይዘት ያለው መልዕክት አሻግረዋል።
ይኽም ኾኖ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ፣ ግብፅ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ከእርሳቸው መንግሥት ጋር እንዲህ ያለው ጥምረት ውስጥ ልትገባ የምትችልበት አመክንዮ ግልጽ ኾኖ ሳለ፣ ሊከላከሉላት ረዥም ርቀት ከመጓዝ ግን ወደኋላ አላሉም፡፡ ይኽንንም ‹‹ግብፅ የራሷ የሆነ አተያይ እና ምርጫ አላት። መገናኘታችንም ኾነ መወያየታችን ፈጽሞ አንዱ ከሌላው ጋር ግጭት ውስጥ ለመግባት የሚያበቃ ተደርጎ መወሰድ የለበትም›› ሲሉ በዐጭሩ የጓዳ ውላቸው ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የወለደው አለመኾኑን ሊያስረዱ ሞክረዋል።
ወዲ አፎም በግልጽ ይኽን ይበሉ እንጂ፣ ዞር ብለው ግን የግብጽ ኹነኛ የትኩረት ዒላማ ስለኾነው የዐባይ ውሃ እና በላዩ እየተገነባ ስላለው የሕዳሴው ግድብ ሁስኒ ሙባረክን አልያም ገማል አብዱልናስርን የሚያስንቅ አስተያየት ከመሥጠት አልተመለሱም፡፡ ለፕሮጀክቱ ያላቸውን አስተሃቅሮ መግለጽ የጀመሩትም የግድቡን ሕጋዊ ሥም ለመጠቀም ባለመፈለግ ጭምር ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ምንም እንኳን ከጥቂት ዓመታት በፊት በነበረው የጫጉላ ጊዜያቸው ኢትዮጵያ ድረስ መጥተው የሕዳሴውን ግድብ በግንባር የጎበኙ ቢኾንም፣ በዚህ ቃለ ምልልሳቸው ግን ልክ የዛሬ ዐሥራ ዐራት ዓመት የግድቡ መሠረተ ድንጋይ ሲጣል ለጥቂት ወራት የፕሮጀክቱ መጠሪያ ኾኖ የቆየውን ‹‹ሜሌኒየም ግድብ›› የሚለውን ሥም መጠቀምን መርጠው ታይተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ኾነች የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግድቡን ግንባታ ያስጀመሩት ልማት ፈልገውም ኾነ 85 በመቶ ድርሻ የሚያመነጨውን ተፈጥሯዊ ጸጋቸውን ፍትሓዊ በኾነ መንገድ ለመጠቀም አስበው ሳይኾን ኾነ ብለው ግብጽን ለመጉዳት ነው ሲሉም ከሰዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ይኽንን ሙግታቸውን ለማጽናት ወደኋላ ሠላሳ ዓመታትን ተመልሰው ከአቶ መለስ ጋር ‹‹አደረግሁት›› ያሉትን የግል ውይይት ከመጥቀስ አንስቶ ፤ የግንባታውን ኢ ፍትሓዊነት ለማጉላት ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ በርካታ ወንዞች እያሏት ዐባይ ላይ ለምን ሙጥኝ አለች?›› እስከማለት ደፍረዋል፡፡
ቃለ ምልልሱን የተከታተሉ በርካቶች፣ በቅኝ መገዛትን ከኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት ተነጥሎ ‹‹ኤርትራዊ›› የተሰኘ ማንነትን ለማዋለድ ምክንያት በኾነበት ሻዕቢያዊ ብሔረተኝነት ውስጥ፣ የአሥመራው አለቃ ለግብጽ የዓባይ ውሃ ባለቤትነትን ለማስረገጥ አይደለም እንዲህ ያሉ ስንኩል አመክንዮዎችን፣ የ1929ኙን እና የ1959ኙን የቅኝ ግዛት ውሎች እማኝ አድርገው ለመጥቀስ ቢታትሩ እንኳን አያስገርምም ይላሉ፡፡ እንኳንስ ስትራቴጂያዊ ጥቅማቸው ግዘፍ የሚነሱትን ምጽዋ እና አሰብ ወደቦችን ቀርቶ ባድመን ለመሰለች የበሬ ግንባር ለምታህል መሬት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ወደ ሞት ቀጣና ለማጋዝ ሁለቴ ማሰብ ያላስፈለጋቸው ኢሳይያስ፣ ኢትዮጵያ ሥር ነቀል የኢኮኖሚ ለውጥ አመጣበታለሁ ያለችውን ትልቁን የተፈጥሮ ሃብቷን በፍትሓዊነት እና በመግባባት መንፈስ ለመጠቀም የሔደችበት ርቀት በዚህ መጠን አልዋጥላቸው የማለቱ አመክንዮ የመነጨው በርግጥም ቅኝ ተገዢነት ከሚወልደው ተነጣይነት ካልኾነ ከሌላ ከምንም ሊኾን አይችልም መባሉ ውሃ የሚያነሳ መከራከሪያ ነው፡፡
በርካቶች እንደሚሉት በዚያ የፕሬዝዳንቱ ቃለ ምልልስ በግልጽ የተካደው የጸረ ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ስምምነት ግን፣ አሁንም ቢኾን በቀንዱ ኢትዮጵያ ላይ እንደ እርኩም የሚያንዣብበውን ሥጋት ባዶ አያደርገውም፡፡ ኤርትራ በዚህ መጠን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን ፍትሓዊ በኾነ መንገድ አልምታ ከመጠቀም መብቷ በዐደባባይ ተቃራኒ የመቆሟ ሀቅ የሚያስረግጠውም ይኽንኑ ነው፡፡ ምንም እንኳን የሩቅ ጎረቤቷ ግብጽ ላለፉት ዐሥራ ዐራት ዓመታት በግድቡ ግንባታ ላይ ተመሳሳይ የማሰናከያ ስትራቴጂዎችን ከመከተል ታቅባ ባታውቅም፣ በተግባር ግን ጫና የመፍጠር ዕድሏ ያሽቆለቆለ ኾኖ ታይቷል፡፡ ይኽ በተደጋጋሚ ማስፈራራትን ማዕከል ያደረገው ፖሊሲዋም ቢኾን፣ በኢትዮጵያ በኩል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባስቀመጡት ‹‹ያለመፍራት ፖሊሲ›› ምክንያት ይኼ ነው የሚባል ተጽዕኖ ሳያሳድር ዛሬ ደርሷል፡፡ ለዚህም ይመሥላል፣ የቅርቡ ግብጽ ከኤርትራ እና ሶማሊያ ጋር አሥመራ ላይ የተፈራረመችው ፊርማ ቀለም ሳይደርቅ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጥታ ተነጋግራ ችግሩን ለመፍታት ፍላጎት እንዳላት መግለጽ ውስጥ የገባቸው፡፡ ነገሮች በዚህ መልክ ለኢትዮጵያ እያጋደሉ ቢመስልም፣ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ሰሞነኛ ቃለ ምልልስ ግን፣ ኤርትራ የቱን ያህል ከኢትዮጵያ ስትቴጂያዊ ጥቅም በተቃራኒው መቆሟን እርግጥ አድርጎ ያለፈ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 220 ታህሳስ 12 2017 ዓ.ም
