የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኝን ግዙፍ ክፍል “የግጭት ዞን” የሚል ምድብ ውስጥ እንዳስገባው በመግለጽ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጠ።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ ነዋሪዎች ከድንበር 40 ኪሎ ሜትር ገደማ በዛህራኒ ወንዝ ሰሜን አቀጣጫ እንዲጓዙ አሳስቧል።
ጦሩ እጅግ ከባድ የሆነ የኃይል እርምጃ እንደሚወስድ ያስታወቀ ሲሆን፤ ሄዝቦላህ በተደጋጋሚ የተኩስ አቁሙን ጥሷል በሚል ከስሷል።
የተኩስ አቁሙ ከታወጀ ከሚያዚያ መጀመሪያ ወዲህ 14 በመቶ የሚሆነውን የሊባኖስ ግዛት ከሚሸፍነው አካባቢ ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ ሲጠየቅ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ረቡዕ ዕለት እስራኤል በደቡባዊ ጣይር ከተማ ድብደባዎችን ፈፅማለች። እስራኤልን የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ የሚከስሰው ሄዝቦላህ ተዋጊዎቹ ከእስራኤል ወታደሮች ጋር መጋጨታቸውን ተናግሯል።
የረቡዕ ጥቃት የመጣው ሄዝቦላህ በሊባኖስ ግዛት በሚገኙ ወታደሮች እና በሰሜናዊ እስራኤል ንፁሃን ላይ የድሮን ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የምድር ዘመቻቸውን እንደሚያስፋፉ ካስታወቁ በኋላ ነው።
ባለፉት 24 ሰዓታት የእስራኤል ጦር ዘጠኝ የአካባቢውን ለቃችሁ ውጡ መመሪያዎችን አውጥቷል። ይህም በእስራኤል-ሊባኖስ ድንበር ግዙፍ ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት የደቀነ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎችንም እንደሚያፈናቅል ተገምቷል።
