እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታል !
“ጽዮን” የሚለው ቃል ትርጓሜው “ጸወን አምባ መጠጊያ” ማለት ነው፡፡ አንድም በምሥጢሩ ሲፈታ “ማሕደረ አምላክ” ማለት ነው፡፡ ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለቅድስት ድንግል ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስት ያገለግላል፡፡
“እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ። ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ። አሮጊቶችዋን እጅግ እባርካለሁ፥ ድሆችዋንም እንጀራ አጠግባለሁ። ካህናቶችዋንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለሁ፥ ቅዱሳኖችዋም እጅግ ደስ ይላቸዋል።
” የሚል ኃይለ ቃል በመዝ 131÷13 ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ኅዳር 21 ቀን ጽዮን ማርያም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል ነው፡፡ በዚህ ቀን ታቦተ ጽዮን፣ ጽላተ ኪዳን ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ መሰጠቷን እናስባለን።
በሊቀ ካህኑ ኤሊ ዘመን ታቦተ ጽዮን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ ኢሎፍላውያን እጅ ተማረከች፡፡ እነርሱም ታቦተ ጽዮንን ዳጐን በተባለው ጣኦታቸው ቤት ውስጥ አመሻሽ ላይ ታቦቷን ከስር ጣኦቱን ከላይ አድርገውት ቢሔዱም ማለዳ ሲመጡ ዳጎንን ጥላው በላዩ ላይ ተቀምጣበት አገኙ፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ እንደቀድሞው ቢያስተካክሉም በሦስተኛው ቀን ግን መሬት ላይ ጥላው በግንባሩ ተደፍቶ ሲሰግድላት አጊኝተውታል፡፡ ሀገራቸው በእባጭ በሽታ በመመታቱም ታቦተ ጽዮንን ከእጅ መንሻ ጋር ወደ ሀገሯ ሸኝተዋታል፡፡
1ኛ ሳሙ. 5÷1 ተጽፎ የምናገኘው ይሕ ታሪክ በየዓመቱ ኅዳር 21 በደማቅ ሥነ ስርዓት በአክሱም ጽዮን ይከበራል፡፡ በዘመነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በአሚናዳብ ሠረገላ ሁና ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ቅዱሱ ንጉሥ በታላቅ ሐሴት በፊቷ ዘመረ፤ አገለገለ።
ምድራዊ ክብሩን እስኪረሳ ድረስ ለታቦተ አምላክ ተቀኘላት። በዚህም ምክንያት ሚስቱ ሜልኮል ንቃው ማኅጸኗ ተዘግቷል እስክትሞትም ደረስ አልወለደችም ነበር እንዲል።
ይህንም በ1ኛ ዜና መዋዕል 15÷23 ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ በቅዱስ ሰሎሞን፣ መፍቀሬ ጥበብ ዘመንም ግሩም የሆነ ቤተ መቅደስ ተሰርቶላት ስትገባ ታላቅ ሐሴት ሆኖ ነበር። እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ንጉሱን አነጋግሮ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ንጉስ ሚኒሊክ ዕብነ ሐኪም ታቦተ ፅዮንን ይዞ ገብቷል።
በዘመነ አፄ ባዜን በ4ኛው መ.ክ.ዘ አማናዊት ጽዮን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ አክሱም ፅዮን በስደት መጥታ ገብታለች። በዚህም ጊዜ ሁለቱ ጽዮኖች ታቦተ ጽዮንና ጽዮን የምትባል ቅድስት ድንል ማርያም ሲገናኙ አክሱም ከክብራቸው የተነሳ በብርሃን አሸብርቃለች። በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአብርሃ ወአፅብሓ ዘመን አስራ ሁለት መቅደስ ያሏትን ቤተ መቅደስ ለእመብርሃን ሰርተዋል በጌታችንም ተቀድሷል።
በአረመኔዋና የቤተ ክርስቲያን ቀንደኛ አውዳሚ በሆመችው በዮዲት ጉዲት ቤተ መቅደሷ ስትፈርስ ወደ ዝዋይ ትሰደድ ነበር በኋላም ቤተ መቅደሷ ሲሰራ ተመልሳ እንደመጠችም በኅዳር 21 ቀን ትከበር ነበር። ኅዳር 21 ቀን በደማቅ ስነስርዓት ስናከብር እነዚህን ድንቅ ተአምራትና ታሪኮች እናስባለን።
እንግዲህ ከፍጡራን ሁሉ በላይ ከፈጣሪ በታች የሆነች እናታችንን ስናስብ “ቅድስት” ማለታችን እንደሌሎች ቅዱሳን በእኩል ደረጃ እያሰብን ሳይሆን ትርጉሙ ይለያል፣ የእርሷም ቅድስና ልዩ ነውና ቅድስተ ቅዱሳን ንፅሕተ ንፁሓን ብርክት እምብሩካን ኅሪት እምኅሩያን እያልን እንጠራታለን።
ገዳማውያኑም ዘወትር ጽዮን እናታችን ሆይ ምልጃሽ አይለየን፣ ጥበቃሽ አይራቀን እያሉ ይጠሯታል፡፡ ገዳማቸውን እንደግፍ በዓታቸውን እናጸና ከበረከታቸው እንሳተፍ፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391 ወይም አቢሲኒያ ባንክ 141029444
ለበለጠ መረጃ:- 09 38 64 44 44/0918077957
