ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
የግንቦት 2017 ዓ.ም ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መጀመርን አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ያስተላለፉት የጉባኤው መክፈቻ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል።
“ረከብነ ጸጋ ወተሰየምነ ሓዋርያተ ከመ ናስምዖሙ ለኣሕዛብ ወይእመኑ በስሙ፡- ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሓዋርያነትን ተቀበልን” (ሮሜ.፩÷፭)፤
ይህ ሐዋርያዊ ኣስተምህሮ የኛን ተእልኮና ተልእኮው ያስፈለገበትን ምክንያት ኣጉልቶ ያሳያል፤ የተቀበልነው ስጦታም ምን ያህል ታላቅ እንደ ሆነ ምንባቡ ያስረዳል፤ ሓዋርያው በዚህ መልእክት የቅዱስ ወንጌል ኣስተምህሮ ዋና ግብ ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ማድረግ ነው በማለት ያስተምረናል፤ እውነት ነው ድሮውኑም ቢሆን ለእግዚኣብሔር መታዘዝ ኣቅቶን ነው የወደቅነው፤ ዛሬም የምንነሣው ከእምነት የተነሣ መታዘዝን ገንዘብ ስናደርግ ነው፤ ከሁሉ በፊት እምነት ይቀድማል፤ ከሱ በኋላ ደግሞ ለእምነቱ በሙሉ ልብ መታዘዝ ይከተላል፤ ይህ ሲሆን መዳንና ትንሣኤ ይገኛል፤ ዓለም በእግዚአብሔር እየተደረገላት ያለ ጥሪ ይኸው የመታዘዝ ጥሪ ነው፤
ይህንን መለኮታዊ ጥሪ ለዓለም የማድረስ ኃላፊነትም ለኛ ለቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት የተሰጠ እንደሆነ ሐዋርያው አስገንዝቦኣል፤ ኃላፊነቱ ሲሰጠን ከነመሳርያው ነው፤ እሱም ጸጋና ሓዋርያነት ነው፤ እኛም እሱን ተቀብለናል፤ እንግዲያውስ የተቀበልነውን ጸጋና ሓዋርያነት በዓለም ውስጥ ላለው ሕዝበ እግዚአብሔር ኣገልግሎት ማዋል ከኛ ይጠበቃል፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣበላት!!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በአሁኑ ጊዜ የሌለበት ክፍለ ዓለም የለም፤ ምክንያቱም የዚህ ሲኖዶስ ወኪሎች ሊቃነ ጳጳሳት በኣፍሪካ፣ በኣውሮፓ፣ በሰሜን ኣሜሪካ፣ በላቲን ኣሜሪካ፣ በካናዳና በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያና በኣውስትራሊያ ወዘተ የሚገኙ ሕዝበ እግዚአብሔር ምእመናንን በማገልገል ላይ ይገኛሉና ነው፤ ይህ ዕድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መለኮታዊ ተልኮውን በአጽናፈ ዓለም ሁሉ ለማድረስ ምቹ መደላድል ፈጥሮለታል፡፡ከዚህም በመነሣት በየክፍለ ዓለሙ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃነ ጳጳሳት ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሻገር የየአካባቢውን ሕዝብ በማስተማርና በማቀፍ የተጣለባችሁን ሓዋርያዊ ተልእኮ በትጋትና በንቃት መወጣት ይኖርባችኋል፡፡
በማእከል ሆኖ እየመራ የሚገኝ ቅዱስ ሲኖዶስም ለዚህ ተልእኮ ምቹ መደላድል የመፍጠር ኃላፊነቱን በኣግባቡ መወጣት ይገባዋል፡፡ በተለይም ትምህርተ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የተማሩና በጥልቀት የተገነዘቡ፣ ብስለትም ያላቸው፤ እንዲሁም በቋንቋና በሥነ ልቦና ዕውቀት የላቀ ሀብተ ጸጋ ያላቸውን በሐዋርያነት እያሠለጠነ በአጽናፈ ዓለም ሁሉ ሊያሰማራ ይገባል፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣበላት!
በብሂለ አበው (ፀሐይ ለመስኮቷ ሳታበራ…) እንደሚባለው ለሌላው በብቃት መድረስ እንችል ዘንድ እኛ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሲኖዶሱ መንበር በሚገኝባት ምድረ ኢትዮጵያ ከመቸውም የተሻለ ስራ በመስራት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ሕዝቡንም ማገልገል ይገባናል፤ ሁላችንም እንደ ምንገነዘበው በሲኖዶሳችን ያልታቀፉ ብዙ ወገኖች በሀገር ውስጥ ኣሉን፤ እነዚህ ወገኖች አንዳንዶቹ በተለያየ ምክንያት ከኛ የወጡ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የሄዱት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ፣ ሌሎችም ወደ መንጋው እንዲቀላቀሉ በርትቶ መስራት የዚህ ጉባኤ ተቀዳሚ ተልእኮ ነው፤ ምክንያቱም ጸጋንና ሐዋርያነትን የተቀበልንበት ዋናው ምክንያት ይህንን ለማድረግ ነውና፡፡ ከዚህ አኳያ የቤተ ክርስቲያናችን ተደራሽነት በሳሳበት ኣካባቢ ሁሉ የተለየ ትኵረት ሰጥተን መስራትና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውሉደ ክህነትና ምእመናን የሆን ሁላችን፣ ከሁሉ በፊት ያለንን ዓቅምና ብቃት በኣግባቡ መገንዘብ ይኖርብናል፤ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሁንና ለፈጣሪው በቈራጥነት የሚታዘዝ ምእመን፣ ወጣት፣ ካህን ኣለን፤ ይህ ትልቅ ጸጋ ነው፤ ይህንን ጸጋ እግዚአብሔር፡ ለእግዚአብሔር መንግሥት በሚመች ሁናቴ ዝቅ ብሎ ማገልገል የክብር ክብር ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሓቅ፣ በቅንነት፣ በትጋትና በታማኝነት ቆመን ካገለገልነውና ኣባትነታችንንና መሪነታችንን በመልካም አሰራር በትክክል በኅሊናው እንዲቀረጽ ካደረግን፣ ይህ ኃይል ከጐናችን እንደማይለይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ይህንን ካሳካን ለኛ የተሰጠ ኃይልና ብቃት በየትም ኣይገኝም፡፡
በዚህም በዚያም ሃይማኖቱ የሚጠይቀውን ሰብእና እና ቁመና ይዘን ከተገኘን፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ያለውን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን ሳይቀር ለመስጠት ወደ ኋላ የማይል የእግዚአብሔር ሕዝብ ኣለን፤ ስለዚህ ይህንን ማሳካት እንችል ዘንድ ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንድናስገኝ የተቀበልነውን ጸጋና ሐዋርያነት በክብር እንያዝ፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!!
ለሕዝበ እግዚአብሔር የምናበረክተው ኣገልግሎት በመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚውና በማኅበራዊው ኣገልግሎትም ጭምር ነው፤ ከዚህ ኣንጻር ሕዝባችን የተሻለ ማኅበራዊ ኣገልግሎት እንዲያገኝ፣ በኢኮኖሚውም ከድህነት የተላቀቀ እንዲሆን፤ እንደዚሁም ሰላሙና ኣንድነቱ የተጠበቀ እንዲሆን፣ በማስተማርም በተግባር በመሳተፍም የሕዝቡ መሪዎችና ኣርኣያ ሆነን መስራት ይገባናል፤በተለይም ከሰላም እጦት የተነሣ በእጅጉ እየተጎዳ ያለውን ሕዝባችን ሰላምና ፍትሕ እንዲያገኝ በጸሎትም በትምህርትም፣ በምክርም ተግተን መስራት ኣለብን፤
እንዳጋጣሚ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእንግልት የተላቀቀበት ጊዜ ብዙ እንዳልሆነ ይታወቃል፤ ለእንግልት እየተዳረገ ያለውም የሌሎች እጅ ባይለየውም በዋናነት በገዛ ልጆቹ ነው፤ እናት በገዛ ልጆቿ ስትንገላታ ማየት እጅግ ኣሳዛኝ ነገር ነው፤ እንደዚህ ያለው ነገር በደንብ ያልታሰበበት ኣካሄድ በብስለትና በንስሓ ማስተካከል አሸናፊነትን እንጂ ተሸናፊነትን አያሳይምና እንዲታሰብበት እንመክራለን፤ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ልማትና ዕድገት እናሻግራለን ብላችሁ እየደከማችሁ ያላችሁ ወገኖቻችን እባካችሁ መለስ ብላችሁ እናታችሁ
የተንገላታችበትን እዩና በቃ በሉ፤ሁሉን የሚያግባባ ነገር ፈልጉና ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ፍቱ፤ በዚህ ኣማራጭ እናት ሀገር እፎይታ እንድታገኝ ኣድርጉ፤ ይህንም ለውድ እናት የሚደረግ ካሣ ኣድርጋችሁ ውሰዱት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጥሪም ይህ ነው፤
በመጨረሻም የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ኣስተዳደራዊ ኣፈጻጸማችን በመገምገም ለቀጣዩ ጊዜ የስራ ኣቅጣጫን የሚያስቀምጠው የረክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተጀመረ መሆኑን ለኦርቶዶክሳውያን ሕዝበ ክርስቲያን እናበስራለን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣
ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
