አስቴር አሥራት
አስቴር አሥራት የ18 ዓመት ወጣት ናት፡፡ ኑሮዋ በዲላ ከተማ ሀሮወላቡ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሲኾን፣ የ9ኛ ክፍል ተማሪም ናት፡፡ አስቴር ከቤተሰቦቿ ጋር እየኖረች ትምህርቷን በመከታተል ላይ የምትገኝ ቢኾንም፣ በአንድ ወቅት እናቷን በሞት ያጣችበት አጋጣሚ ግን፣ በኑሯቸው ላይ ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ፈጠረ፡፡ በዚህም ምክንያት አስቴር መደበኛ ትምህርቷን ለመቀጠል ተቸገረች፡፡ ትምህርቷን በማቆም እና በመቀጠል ግራ አጋቢ ሁኔታ ላይ የወደቀችው አስቴር ግን፣ ከዕለታት በአንዱ ስለ ከፍታ ፕሮጀክት አንዳች ጠቃሚ መረጃዎች ጆሮዋ ደረሰ፡፡ እርሷም ወደ ቡድኑ በመሔድ ከከፍታ ቡድን አባላት ገንቢ የተባለ ምክር እና ሐሳብ ማግኘት ቻለች።
አስቴር ከፍታ ተከታታይ እና መልከ ብዙ የክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን ማለትም፣ በሕይወት ክህሎት፣ በፆታዊ እና ሥነ ተዋልዶ ጤና ዙርያ፣ በቢዝነስ ሥራ ክህሎት፣ ፋይናንስን በተመለከተ ግንዛቤ፣ እንዴት ንቁ ዜጋ መኾን እንደሚቻል፣ በሥራ ፈጠራ፣ በማማከር እና በውጤታማ የሥራ ባሕል ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን በወጣቶች ማዕከላት እንደጀመረ ስትሰማ ለመቀላቀል አላመነታችም፡፡ በመኾኑም ከፍታ የሚሰጣቸውን እነኚህን የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ተከታትለው ከወሰዱ ሠልጣኞች መካከል አንዷ ለመኾን በቃች።
ከከፍታ ያገኘችው ጠቃሚ ሥልጠና ታዲያ አስቴር ሥራ ማግኘት የምትችልባቸውን መንገዶች ለማወቅ ክህሎቱን ቸራት፡፡ በዚህም የተነሣ ሥራ ለማግኘት ተቀምጦ መጠበቅ አልያም የሥራ ማመልከቻ አስገብቶ ምላሽ መጠበቅ ትክክለኛ መንገድ አለመኾኑን ተረዳች፡፡ አስቴር በዚህ ረገድ ያመጣችው ትልቅ የአመለካከት ለውጥ ጠቅሟታል፡፡ ዛሬዋን ብቻ ሳይኾን የነገዋን ሕይወት እንዴት በዕቅድ መምራት እንዳለባት ግንዛቤ አግኝታለች፡፡ በተጨማሪም በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ባለ የሥራ መስክ ላይ ተሰማርታ ጎን ለጎን ትምህርቷን መቀጠል እንደምትችል አምናለች፡፡
አሁን ላይ አስቴር ዕቅዷን በተግባር መተርጎሟን አስመልክታ ስትናገርም፣ ‹‹…የከፍታ ቡድን አባላት ድጋፍ ሕይወቴን ለመምራት እና ለችግር የተጋለጡ ቤተሰቦቼን ለመርዳት በአንድ የግል ዘርፍ ውስጥ ተቀጥሬ እንድሰራ ስንቅ ኾኖኛል…›› በማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ አስቴር አሥራት ትምህርቷን ለመቀጠል ሙሉ ፍላጎት ያላት ሲኾን፣ የተሻለ ሥራ እስክታገኝ ድረስም በጽዳት ሙያ እየሠራች የምትቀጥል ይኾናል። አስቴር የከፍታ ቡድን አባላት አሁን ላይ ለተሰማራችበት የሥራ መስክ እንድትበቃ ሁኔታዎችን ስላመቻቹላትም የከበረ ምሥጋናዋን ታቀርባለች፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 220 ታህሳስ 12 2017 ዓ.ም
