‹‹ከፍታ በጨለመብን ሰዓት የደረሰ ብርሃናችን ነው››

Date:

አዲሱ ቡሹራ

አዲሱ ቡሹራ ይባላል፡፡ የ27 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ውልደቱና ዕድገቱ አለታ ጩኮ በተባለች ገጠር ነው፡፡ ይኹን እንጂ ቤተሰቡ ባለባቸው ኢኮኖሚያዊ ዐቅም ውሱንነት ሳቢያ የቀለም ትምህርት መከታተል አልቻለም፡፡ ለቤተሰቡ የበኩር ልጅ እንደመሆኑ መጠንም ገና በጊዜ በጥቃቅን የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በመሠማራት በድህነት ውስጥ ያሉትን ቤተሰቦቹን በገንዘብ ለመደገፍ ትልቅ ኃላፊነት ወሰደ። በዚህ ከቤተሰቡ በተረከበው ኃላፊነት እየሠራ በነበረባቸው ጊዜያት ግን አንድ ችግር ገጠመው፡፡ አዲሱ በአንድ ወቅት ከሞያሌ – ሀዋሳ መስመር ሕገወጥ በኾነ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፉ በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህልም ለእሥር ተዳረገ፡፡

አዲሱ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ መገኘት ፈጽሞ የልጅነት ሕልሙ እንዳልነበረ ይናገራል፡፡ ነገር ግን አለመማሩ እና በዚህም ሳቢያ ስለ ሕይወት አማራጮች ባለው የግንዛቤ ማነስ ምክንያት ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለመሠማራት መገደዱን ይገልጻል፡፡ እንዲህ ያለው ታሪክ በሀዋሳ ማረሚያ ቤት ያሉ አብዛኞቹ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች የሚጋሩት ነው፡፡

አዲሱ እንደሚለው፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ካሉት የዕድሜ አቻዎቻቸው በተለየ፣ በእስር ላይ የሚገኙት አብዛኞቹ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች መሠረታዊውን የመጻፍ እና የማንበብ ትምህርት እንኳን አያገኙም፡፡ በዚህም ምክንያት የነገ ዕጣ ፈንታቸውን አስመልክቶ ያላቸው ተስፋ የመነመነ አድርገው ስለሚያስቡ ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ የእሥር ዘመናቸውን የሚያሳልፉት በጭንቀት ውስጥ ነው፡፡ በዚህ መሃል ግን የከፍታ ፕሮጀክት ሀዋሳ ቅርንጫፍ፣ ለእነኚህ በማረሚያ ቤት ለሚገኙ ወጣቶች ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉበትን መርሃ ግብር ነድፎ ወደ ሥራ ገባ፡፡ ይኽም በቁጥር 82 የሚኾኑ ወጣቶች (ከእነዚህ መሃል 30 ያህሉ ሴቶች ናቸው) የማንበብ እና የመጻፍ ክህሎት ቀስመው ከእሥር ሲወጡ ያለውን የነገ ሕይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ ተመዘገቡ፡፡ ከእነዚህም ተመዝጋቢዎች መካከል አንዱ ደግሞ አዲሱ ቡሹራ ነበር።

አዲሱ እንደሚለው፣ እርሱም ኾነ ሌሎች የእሥር ቤት ወዳጆቹ የከፍታ ፕሮጀክት ያቀረበላቸው ይኽን የመጻፍ እና ማንበብ ክህሎት ሥልጠና፣ አሁን ባሉበት ዕድሜ በሕይወታቸው ውስጥ እናገኘዋለን ብለው ያሰቡት ዕድል አልነበረም፡፡ ኾኖም በተግባር የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ኾነው፣ ከማንበብና መጻፍ ባሻገርም መሠረታዊ የሒሳብ ስሌቶችን አውቀው ሕይወታቸውን የሚቀይር ዕውቀት ቀስመዋል።

በዚህ የትምህርት መርሐ ግብር በደረጃ 1 ከተመዘገቡት መካከልም 52 የሚኾኑት ተማሪዎች ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ ደረጃ ሁለት ያለፉ ሲሆን፣ እነዚህም ወጣቶች ወደፊት ሕይወታቸውን ለመለወጥ የሚያግዟቸውን ሌሎች የከፍታ አገልግሎት ፓኬጆች ሥልጠና ለማግኘት ጥያቄ ከማቅረብ ወደኋላ አላሉም፡፡

የከፍታ ፕሮጀክትም በሥሩ ባለው የጎልማሶች ትምህርት ፕሮግራም አመቻችነት፣ ለእነኚሁ ወጣቶች ተጨማሪ የሕይወት ክህሎትና የሥራ ፈጠራ ሥልጠና የሰጠ ሲሆን፣ ከሥልጠናው በኋላም በማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የከተማ ግብርና እንዲጀመር ውሣኔ ላይ ደረሰ። ይኽንን ውሳኔውን በመያዝም፣ ወደ ማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በመቅረብ ለግብርና የሚኾን ቦታ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን፣ አስተዳደሩም ሐሳቡን በመደገፍ ለዚህ ተግባር የሚሆን ቦታ አበርክቷል። ወጣቶቹም ይህንን ቦታ ለማልማት እስካሁን ከ15,000.00 ብር በላይ በመቆጠብ መሬቱን ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ። አዲሱም ከዚህ የከተማ ግብርና ሥራ በተጨማሪ የእሥር ጊዜውን ጨርሶ ሲወጣ፣ ገቢ የሚያገኝበትን አማራጭ ለማስፋት በማሰብ ከወዲሁ  በማረሚያ ቤቱ የፀጉር አስተካካይነት ሥራን ጀምሯል።

በመጨረሻም አዲሱና ጓደኞቹ ጨለማ ከመሰላቸው ነገ አውጥቶ ብሩህ ተስፋ እንዲያሳድሩ እና በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲያድርባቸው ላደረጋቸው፣ ይኽንም መሠረታዊ በሚባል ትምህርትና ሥልጠና ለሰጣቸው ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› ፕሮጀክት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል። አዲሱና ጓዶቹ የመሠረቱት የልማት ቡድንም ዓላማው አሁን ያለውን የከተማ ግብርና እንቅስቃሴ በማስፋት በቀጣይ እንደ አንድ የንግድ ድርጅት የሚታይ ማኅበራዊ ኢንተርፕራይዝ መመሥረት መሆኑንም ይገልጻሉ።

———-

ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 218 ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የምርጫ ካርድ፡ የአገር ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ

ግዮን መጽሔት :- በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዞ ውስጥ ምርጫዎች የሥልጣን...

አደይ ኢትዮጵያ ጓል አስመራ…!!

የቀድሞ ፕ/ት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የስንብት ቃል ለጠቅላይ ሚ/ር ዐብይ...

ትራምፕ ከኢራን ጋር በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ሁለተኛው ዙር ድርድር ሊደረግ እንደሚችል ተናገሩ

ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር...

በ”ፊንቴክ” ኢንቨስትመንት በተጠረጠሩት ላይ ተጨማሪ ጊዜ ተፈቀደለት

ፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀን ለምርመራ እንዲፈቀድለት ባለፈው አርብ በነበረው...