ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምህርት ዕድልና ስኮላርሺፕ የሚያገኙበት “ኢትዮ-ዓለም አቀፍ የወጣቶች የትምህርትና ቴክኖሎጂ ፌስቲቫል” በታሪካዊው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ፓን አፍሪካ አዳራሽ በድምቀት እየተካሄደ ይገኛል።
ከየካቲት 14 እስከ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ፣ ተማሪዎች ከ100 በላይ ከሚሆኑ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ተቋማት ጋር በቀጥታ የመገናኘት ብርቅዬ ዕድል አግኝተዋል።
የፌስቲቫሉ ዋና ዓላማ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ የሚፈልጉበትንና የምዝገባ ሂደቶችን የሚያሳልጡበትን መረጃ በቀላሉ እንዲያገኙ ማድረግ ሲሆን፣ በተለይም እንደ ካናዳ እና አሜሪካ ካሉ ሀገራት የመጡ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች በተቋሞቻቸው ያሉትን ሰፊ አማራጮች እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
ይህ መድረክ ተማሪዎች በትምህርት ፍለጋ የሚያጋጥሟቸውን ቢሮክራሲያዊ ውክባዎች በመቀነስ፣ የወደፊት የትምህርት ሕይወታቸውን በአንድ ማዕከል እንዲያመቻቹ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በፌስቲቫሉ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፣ ይህ መድረክ ወጣቶችን ከዓለም አቀፍ የዕውቀት ዑደት ጋር የሚያገናኝ ወሳኝ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ድልድይ ነው። ፌስቲቫሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርትን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም ተጠቁሟል።
