ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ፣ከእንስሳት ወደ ሰው እና ከእንስሳት ወደ እንስሳት የሚተላለፉ ሲሆን ከ7ዐ% በላይ የሰው ልጅ ተላላፊ በሽታዎች ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታውቋል ።
ተላላፊ በሽታዎች በብዛት ያላደጉ ሀገራትን እንደሚያጠቃ እና በኢትዮጵያም ከ60 %በላይ ህመሞች በተላላፊ በሽታዎች አማካኝነት እንደሚመጡ ተገልጿል።
የፀረ-ተዋህስያን መድሃኒቶች ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከልና በማከም የበርካታ ሰዎችን ህይወት ማትረፍ የቻሉ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የፀረ-ተዋህስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ አሳሰቢ ከሆኑ ዓለም አቀፍ ችግሮች አንዱ እየሆነ እና በበርካታ ሀገራትም የጤና፣ኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮችን እያስከተለ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከሚያጋጥሙ ክፍተቶች መካከል የእቅድ አፈጻጸም ጉደለት፣ የባለሙያው መመሪያ አተገባበር ጉድለት እና የህገወጥ መድሃኒት አጠቃቀም ቁጥጥር ክፍተት ተጠቃሽ መሆናቸውን ጣቢያችን ሰምቷል።
እንዲሁም በቂ የምርምር ተደራሽነትና የምርምር ውጤቶችን የመጠቀም ክህሎት አለመኖር ሌላኛው ክፍተት ነው ተብሏል ።
ችግሩን ለመቅረፍም የተላላፊ በሽታዎች መከላከል እና ቁጥጥርን እንዲሁም በሰዎች ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑ ተነግሯል ።
