ኪሳራ ላይ በመሆኔ ‘አማራጭ አነስተኛ የገቢ ግብር’ ሊጣልብኝ አይገባም

Date:

የ15 ዓመታት ውል አስሮ በኢትዮጵያ እየሰራ የሚገኘው ሳፋሪኮም፤ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሼ እየሰራሁ የምገኘው የቴሌኮም ሥራ አትራፊ የሚባል ደረጃ ላይ ባለመድረሴ፤ ‘አማራጭ አነስተኛ የገቢ ግብር’ ሊጣልብኝ አይገባም ሲል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ይህ የተባለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ  ዙሪያ ይፋዊ ውይይት መድረክ በምክር ቤቱ የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዘጋጅነት በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

በምክር ቤቱ ውይይት ከተካሄደባቸውና ጥያቄ ካስነሱ ጉዳዮች መካከል አማራጭ አነስተኛ የገቢ ግብርን የተመለከተው ይገኝበታል።

በረቂቁ ላይ “አማራጭ አነስተኛ የገቢ ግብር ማናቸውም በንግድ ሥራ ላይ ያለ ሰው ለዓመታት በኪሳራ ሊቀጥል እንደማይችል ግልጽ ነው” ይላል።

በሌላ በኩል “ምንም ያልሰራ ከሆነ ወደ ኪሳራ የሚቀየር እንጂ ባለበት የሚቀጥል ሊሆን አይችልም” ይልና፤ “በመሆኑም የተደረገው ጥናት ግብር ሳይከፍሉ የሚሰሩ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን የሚያሳይ ነው” ብሏል።

በመሆኑም በዚህ አይነት የሚያጋጥመውን ችግር ለመፍታት ሀገሮች የሚጠቀሙበት አስራር ማናቸውም በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ግብር ከፋይ ከስሮ የንግድ ሥራውን ካልዘጋ በስተቀር፤ ለዓመታት በኪሳራ ሊቀጥል ስለማይችል ከጠቅላላ ገቢው የተወሰነ መቶኛ አማራጭ አነስተኛ ግብር እንዲከፍል ማድረግ ነው ሲል በረቂቁ ላይ ቀርቧል።

ይህንን በሚመለከት በውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ሀሳባቸውን ከሰጡ ተቋማት መካከል የቴሌኮም ድርጅቱ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ይገኝበታል።

ጅርጅቱን በመወከል በምክር ቤቱ የተገኙት አቶ ዳዊት ፍስሀ፤ በአማራጭ አነስተኛ የገቢ ግብር ላይ ያላቸውን ሀሳብ ሰጥተዋል።

አቶ ዳዊት “ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ልዩ የሆነ የኢንቨስትመንት ባህሪ ያለው ድርጅት ነው” ያሉ ሲሆን፤ ለ15 ዓመታት ተዋውሎ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህ ፈቃድ እየታደሰ ለ30 ዓመታት ይቆያል የሚል ተስፋ እንዳላቸው በመግለጽም፤ “ዕቅዶቻችን የረጅም ዓመት ናቸው” ሲሉ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

“ባለፉት 4 ዓመታት ብቻ ከ350 ቢልዮን ብር በላይ ኢንቨስት ያደረገ ትርፍን ብቻ መሠረት ያላደረገ ተቋም ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

“ይሁን እንጂ፤ ይህ ሁሉ የተሰራው የረዠም ግዜ ትርፍ በማሰብ ነው” ያሉት አቶ ዳዊት ፍስሀ፤ “ኪሳራ ገጠመን ብለን ዘግተን አንወጣም፡፡ ውላችንም አይፈቅድም” ብለዋል።

“ሊዘጋ ይችላል በሚል አማራጭ አነስተኛ ግብር ሊጣልብን ብቻም ሳይሆን ኪሳራ ላይ ላለ ድርጅት በፍፁም ተፈፃሚ መሆን የለበትም” ሲሉም ተናግረዋል።

“ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ብዙ ኪሳራ እየደረሰብን የምንሰራውን ኢንቨስትመንት የሚያቀጭጭ ነው” በማልትም ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሌሎች ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ወደ ሀገር እንዳይመጡ እንቅፋት ሊሆን ይቻላል የሚል ሀሳብ እንዳላቸው ተወካዩ አስረድተዋል።

በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ከተመዘገቡት ታክስ ከፋዮች መካከል ከ67 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኪሳራ ወይም ‘ምንም አልሰራንም’ የሚል ማሳወቂያ የሚያቀርቡ ናቸው ሲል ረቂቁ አስቀምጦታል።

ከዚህም በተጨማሪ ምንም አልሰራንም በሚል የሚያስታውቁት ብዛት እየጨመረ ኪሳራ የሚያስታውቁት ቁጥር ደግሞ እየጨመረ መሄዱ ለአማራጭ አነስተና የገቢ ግብር መነሻ መሆኑም ተነስቷል።

(አሐዱ ሬዲዮ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የ8.5 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት በትግራይ ክልል ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ማስከተሉ ተገለጸ

የትግራይ ክልል የፋይናንስ እና ሀብት ትብብር ቢሮ፤ የ8.5 ቢሊዮን...

ኖ ሞር’ ቴአትር በአሜሪካ ለታዳሚ ሊቀርብ ነው

በአገር ውስጥ መድረኮች በነበረው ቆይታ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው...

የሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የዘርፉን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

​​በኢትዮጵያ ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ የሪል ስቴት አልሚዎች እንዳሉ...

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት 54 ‹‹አስገዳጅ›› ህጎችን አፀደቀ

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የደረጃዎች ቦርድ ባካሄደው 5ኛው መደበኛ ስብሰባው፤...