የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባወጣው አዲስ ሪፖርት፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ 500,000 የሚሆኑ ተፈናቃዮች “ከፍተኛ የምግብ፣ የመጠለያ፣ የውሃ፣ የንፅህና፣ የጤና እና የጥበቃ አገልግሎቶች እጥረት” እንደገጠማቸው አስታወቀ።
ወደ 90 በመቶ የሚሆኑት አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በአካባቢው ማህበረሰቦች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ለአጭር ጊዜ በተዘጋጁ ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ናቸው ብሏል። ከእነዚህም መካከል 22,000 ተፈናቃዮች ደብረ ብርሃን እና 10,000 የሚጠጉ ተፈናቃዮች ጃራ መጠለያ ይገኛሉ።
ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ ከምዕራብ ኦሮሚያ ብቻ ከ88,000 በላይ የሚሆኑ ንፁሃን ዜጎች በግዳጅ ተፈናቅለዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል ብዙዎቹ አሁን በደብረ ብርሃን (ቻይና ካምፕ)፣ ወይንሸት እና ባቄሎ በሚገኙ ሶስት መጠለያዎች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች እጅግ የሚጎሉባቸው መጠለያዎች ናቸው ብሏል።
