የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ “በአነስተኛ ክፍያ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት እንልካለን” በማለት ዜጎችን ለማጭበርበር እየሰሩ የሚገኙ ቡድኖች እና ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ማኅበረሰቡ ከዚህ መሰል የማጭበርበሪያ ሐሰተኛ ማስታወቂያዎች ራሱን እንዲጠብቅ እንዲሁም ጥቆማ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዚህም እነዚህን አሳሳች መረጃዎች የሚያሰራጩ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከፍትሕ ሚኒስቴርና ከሌሎች ተዛማጅ የመንግሥት አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ “1 ሺሕ 500 ብር በመክፈል ወደ ካናዳ፣ ሮማንያና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ለመሄድ ምዝገባ ተጀምሯል”፤ የሚሉ ሐሰተኛ መረጃዎችና ማስታወቂያዎች በስፋት መሰራጨታቸውን ተከትሎ “ተቋማችሁ ምን እየተሰራ ነው?” ሲል የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን ጠይቋል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዴስክ ኃላፊ አቶ በዛወርቅ ከተማ በሰጡት ምላሽ፤ ሚኒስቴሩ ከሕግ አካላት ጋር በመተባበር በዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አጥፊዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
አቶ በዛወርቅ ከሀገር መውጣት የሚፈልጉ ሰዎች ትክክለኛውንና አስፈላጊውን መረጃ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማግኘት እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ሕብረተሰቡን ከሐሰተኛ መረጃ ለመጠበቅና ግንዛቤ ለማስጨበጥ በራሱ የማኅበራዊ ድረ ገጽና በመንግሥት ሚዲያዎች ላይ መረጃዎችን በማጋራት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
አሐዱ ራዲዮ
