የኮካ ኮላ ኩባንያ በአሜሪካ የኮላ ምርት ውስጥ እውነተኛ የሸንኮራ አገዳ ስኳር እንዲጠቀም እንዳሳመኑት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡
“ይህ በጣም ጥሩ እርምጃ ነው” ሲሉም ኩባንያውን አመስግነዋል፡፡
የዳይት ኮክ አድናቂ የሆኑት ትራምፕ፤ ከኮካ ኮላ ጋር መነጋገራቸውን ጠቁመው፤ ባቀረቡት ሃሳብ ኩባንያው መስማማቱን ገልጸዋል፡፡
ኮካ ኮላ ለሲቢኤስ ኒውስ በላከው ኢሜል፤ “ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለታዋቂው የኮካ ኮላ ብራንድ ያሳዩትን ጉጉት እናደንቃለን። በኮካ ኮላ ምርት ውስጥ ያሉ አዳዲስ ፈጠራዎችን በተመለከተ ተጨማሪ ዝርዝሮች በቅርቡ ይጋራሉ።” ብሏል፡፡
ኮካ ኮላ ከአሜሪካ ውጭ በተለይም በሜክሲኮ የኮላ መጠጡን የሚያመርተው በሸንኮራ አገዳ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአሜሪካ ግን መጠጡ ከፍተኛ-ፍሩክቶስ ባለው የበቆሎ ሲሮፕ የሚሰራ እንደሆነ በኮካኮላ ድረገጽ ላይ የሰፈረው መረጃ ይጠቁማል፡፡
“በኮካ ኮላ ኩባንያ ውስጥ ያሉትን ሃላፊዎች በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ። በጣም ጥሩ እርምጃ ነው የወሰዱት፡፡ ታያላችሁ – የተሻለ ነው!” ሲሉ ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
ትላንት ረቡዕ የኮካ ኮላ አክሲዮን ሽያጭ፣ በ9 ሳንቲም ወይም 0.13 በመቶ በመቀነስ ወደ 69.27 ዶላር ዝቅ ማለቱ ተዘግቧል፡፡
