ታድለናል፤ የተራራ ሀብታም ሀገር አለን። ሀገሬ ለአፍሪካ ኔፓል ናት። ከሶስት ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው የኢትዮጵያ ተራሮች ብዙ ናቸው። ደግሞ ተራራ ብቻ አይደሉም። እንደ ጋራምባ ባህል አኑረዋል። እንደ ቁንድዶ የዱር ፈረስ ሸሽገዋል፣ እንደ ስሜን ቅዱስ ሰውረዋል፣ እንደ አቡነ ዮሴፍ ሰውና ጭላዳ ታርቆባቸዋል።
የሀገሬ ተራሮች ታሪክ ናቸው። እንደ አምባላጌ ድል ፅፈው፣ እንደ ቧሂት ዘመን ዘክረው፣ እንደ ወህኒ አምባ ታሪክ ሰንደው ይኖራሉ። የእምነት ዓምባ ናቸው ስል እስላምጌን ምስክር ግሸንን ማስረጃ አቅርቤ ነው።
ደግሞ ውበት ናቸው፤ ደጀንና ቱሉ ዲምቱን ያየ ይሄንን አይሞግትም። ምትሃትም ናቸው ጭላሎና ጮቄ ለቆመ የምለው ይገባዋል። ወግ ተሞልተዋል መገዘዝ እና ዳቲ ወለል ገና ተደምጠው አልተጠገቡም።
ኢትዮጵያ ተራራዋ ከሰው አይነጠልም። እንደምን ጉጌ ከጋሞ ይለያል? እንደምንስ ጉናን ከበጌምድር እንነጥለዋለን? ይልቅስ ማማ ናቸው እንደ ሙሳ ዓሊ ሩቅ የምናይባቸው። እንደ አቡዬ ሜዳ ምድር የምንቆጥርባቸው።
ስለ እኛ ይናገራሉ፤ አሲምባ ኢሮብን ይተርካል፣ ዘቢደር የጉራጌ አንደበት ነው፣ አዘሎ አፋርን ያወጋል፣ ጨርጨር ሸጎዬ ያስደምጣል፣ ሙጎ የስልጤ አንደበት ነው፤ ጋራ ሙለታ ደግሞ የሀረርጌ ዜማ። እናም ተራሮቻችን ድምፅ አላቸው።
ዓለም ስለ ተራሮች ደህንነት ይህንን ቀን ስለ ተራራ እናስብ ዘንድ በየዓመቱ ያከብረዋል። የዘንድሮው መሪ ቃል “Glaciers matter for water, food and livelihoods in mountains and beyond.” የሚል ነው።
እኛ ተራራ አለን እንጂ ተራሮቻችን ሰው አለን እንዲሉ አላደረግንም። ይታረዛሉ፣ ይጎሳቆላሉ። ለውሃ፣ ለምግብና ለኑሮ አስፈላጊ ናቸው። የሚለው ምን ያህል እንደ ህዝብ የተረዳነው እንደሆነ አላውቅም። ግን እጠይቃለሁ? ከተራራው በታች የኖርንው በተራራው ፀጋ ነው።
ተራሮች በውሃ ዑደት ውስጥ ሚናቸው ከፍተኛ ነው። የበረዶ ግግር በረዶዎች በቀዝቃዛው ወቅት ውሃ ያከማቻሉ፣ ከዚያም በጸደይና በበጋ ወቅት አቅልጠው ውሃ ይለቃሉ። የዓለም ዋና ዋና ወንዞች የሚጀምሩት በተራራ ሰንሰለቶች ነው። እነዚህ ወንዞች በታችኛው ክፍል ለሚኖሩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኑሮ መሰረት ናቸው።
የአየር ንብረት ለውጥ ይህንን ሚዛን አደጋ ላይ እየጣለ ነው። ግግር በረዶዎች እንደ የውሃ ማማ ሆነው ያገለግላሉ፣ ነገር ግን እየቀለጡ ነው። አንዴ ከጠፉ በኋላ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት ላይ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ ይሆናል።
ያለ ተራሮቻችን የሜዳዎቻችን መልክ ይህንን ባልመሰለ ነበር። ተራሮቻችንን ጥሩ አድርገን ከያዝን ከተራራው በታች ጥሩ ኑሮ እንኖራለን። ተራሮቻችን ቸር ናቸው ትኩረት ነፍገናቸው ህይወት አልነፈጉንም።
ወንዞቻችን የተራሮቻችን ስጦታ ናቸው። ያለ ውሃ ምንም ነን። የሚታረዝ ተራራ ልብስ የማያለብስ ህዝብ ችግር እርቃኑን ያስኬደዋል። እናም ተራሮቻችንን አረንጓዴ ማልበስ አለብን። የተራሮቻችን ጤንነት ከየግላችን ጤና ጋር የተቆራኘ ነው። ለዚህ ነው ስለ ኢትዮጵያ ተራሮች የምጮኽው።
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም – ለድሬ ቲዩብ)
