በትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተመራ ልኡካን ቡድን በለንደን እየተካሄደ ባለው አለም አቀፍ የትምህርት ፎረም 2025 ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ እየተካሄደ ካለው የትምህርት ፎረሙ ጎን ለጎን ከእንግሊዝ የአለምአቀፍ ልማት ሚኒስትር ባሮነስ ቻፕማን ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በዚህም ክቡር ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም የገልጹላቸው ሲሆን በራስ አቅም በ “ትምህርት ለትውልድ’’ ህዝባዊ ንቅናቄ የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ማሻሻን በተመለከተ ስለተገኘው ውጤት አብራርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከሥርዓተ ትምህርት፣ ከመምህራንና የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ስልጠና እና ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ጋር በተያያዘ የተጀመሩ ሥራዎችን ጠቅሰው፣
እነዚህ በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩ ሪፎርሞች በፍጥነት እንዲሳኩ የልማት አጋሮችና በተለይም የእንግሊዝ መንግስት ድጋፉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የእንግሊዝ የአለምአቀፍ ልማት ሚኒስትሯ ባሮነስ ቻፕማን በበኩላቸው በቅርቡ በኢትዮጵያ ያደርጉትን ጉብኝት በማስታወስ በትምህርት ዘርፉ እየተደረገ ያለውን ለውጥ አድንቀዋል፣
የተጀመረውን የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ ምንም እንኳን በእንግሊዝ መንግስት የተደረገው የበጀት ቅነሳ (budget cuts) ቢኖርም በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ የሚካሄደውን ሪፎርም ለመደገፍ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
