የቱሪዝም ሚኒስቴር ቀደም ሲል በሆቴሎችና ሪዞርቶች ላይ ብቻ ሲካሄድ የቆየውን የደረጃ ምዘና ሥራ፣ ሎጆችንና ሬስቶራንቶችን ጭምር እንዲያካትት የሚያስችል አዲስ ሀገራዊ መመዘኛ ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
ይህ አዲስ የደረጃ አሰጣጥ ሥርዓት አገሪቱ ለቱሪዝም ዘርፍ የምትሰጠውን ትኩረት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ የዘርፉን ጥራትና አገልግሎት ለማሻሻል ያለመ ነው ተብሏል።
የተዘጋጀው መመዘኛ በረቂቅ ደረጃ ተጠናቅቆ፣ በቀጣይነት ለባለድርሻ አካላት ውይይት ቀርቦ ተግባራዊ እንደሚደረግ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
በሌላ በኩል፣ ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ አዳዲስ ሆቴሎች በተገቢው ጊዜ የደረጃ ምደባ እንዲያደርጉ የታቀደ ቢሆንም፣ የደረጃ ምደባው ሂደት ላይ ችግሮች መፈጠራቸው ታውቋል።
የተፈጠሩት ችግሮች ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እንዳሏቸው ተጠቁሟል። አንደኛው፣ ባለሀብቶች በተያዘው ጊዜ የኮከብ ደረጃ ለመመደብ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አብዛኞቹ ተቋማት የኮከብ ደረጃ ለመመደብ ብቁ ሆነው አለመገኘታቸው ነው። ይህ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፉን ጥራት ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ላይ ፈተና እንደሚሆን ተገልጿል።
CapitalNews
