እየተዘጋጀ ያለው አዋጅ በሁሉም ክልሎች እና በፌደራል ደረጃ ያሉ ማረሚያ ቤቶች ተመሳሳይ አሰራር እና አስተዳደር እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም በማረሚያ ቤቶች የሚታዩትን ችግሮች በህግ ማዕቀፍ አካትቶ መፍትሔ ለማበጀት ህጉ አስፈልጓል ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልል እና በፌደራል የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ከበጀት፣ ከደህንነትና ጥበቃ እንዲሁም ከአስተዳደር አንጻር የተለያዩ ናቸው ተብሏል፡፡
ህጉ ይህንን የተለያየ አሰራር ወጥ በሆነ አሰራር የታራሚዎችን መብት ለማስጠበቅ የሚያግዝ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ይህ የተነገረው በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሰብዓዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ ላይ ትኩረት የሚያደርገው ዓለም አቀፍ ‘’የኔልሰን ማንዴላ ቀን’’ ለማክበር በተሰናዳ መድረክ ላይ ነው።
ዝግጅቱን በታራሚዎች መብት አያያዝ ላይ የሚሰራው ሴንተር ፎር ጀስቲስ የተሰኘ ድርጅት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደገኛ እፆች እና የወንጀል መከላል(UNODC) የኢትዮጵያ ቢሮ በጋራ ያሰናዱት ነው፡፡
የሴንተር ፎር ጀስቲስ ዳይሬክተር አቶ ኩምሳ ጉተታ በኢትዮጵያ ያለው የታራሚዎች አያያዝ ካለፉት ዓመታት አንፃር መሻሻል ቢያሳይም አሁንም ብዙ የሚቀረው መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተለይም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣውንና የታራሚዎችን ሰብአዊ መብት አያያዝ የሚደነግገውን “የማንዴላ ህግጋት” ላይ ከተዘረዘሩት ዝቅተኛ የሚባሉትን ለማሟላት በብርቱ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ ማረሚያ ቤቶች ከታራሚ አያያዝ ጋር በተገናኘ የሚታዩ ክፍተቶች ለመቀነስ አዲስ ህግ በማስፈለጉ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ረቂቁ በዝግጅት ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ማረሚያ ቤቶች ከበጀት፣ ከደህንነትና ጥበቃ እንዲሁም ከአስተዳደር አንጻር ችግሮች እንደሚታዩ በጥናት መረጋገጡምን ተነግሯል፡፡
በክልል እና በፌደራል የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ከአስተዳደር እና ከከታራሚዎች አያያዝ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ የሚባል ልዩነት መኖሩንም ጥናቱ አሳይቷል ተብሏል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የኮሚሽነር ጄኔራል አማካሪ ረዳት ኮሚሽነር ወንድሙ ጫማ በጥናቱ የተገኙት ችግሮች መንግስት በትኩረት የሚሰራባቸው እንደሆኑ ጠቅሰው እየተረቀቀ የሚገኘው ህግም አንዱ መፍትሔ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የUNODC ኢትዮጵያ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብርሀም አያሌው የታራሚዎችንፍትህ፣ ሰብአዊ መብት፣ እኩልነት እና ክብር እንዲጠበቅ በህግ ማዕቀፍ በመደገፍ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል፡፡
ቀድሞ ከነበረው አሰራር የተወሰኑ መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም ታራሚዎች መብታችን ተጣሰ በማለት የተለያዩ አቤቱታዎችን እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ደግሞ በኢሰመኮ የምርመራና ክትትል ከፍተኛ ዳይሬክር ሜቲ አቶምሳ ናቸው፡፡
ሸገር 102.1
