ማንኮራፋት/Snoring/ በእንቅልፍ ወቅት በአፍ እና በአፍንጫ ውስጥ ያለው የአየር ፍሰት በከፊል ሲዘጋ ይከሰታል፡፡ ይህም በጉሮሮ ውስጥ ያሉት ሕብረ ሕዋሳት እንዲርገበገቡ እና ከፍተኛ ድምፅ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
ማንኮራፋት ከአጠገባቸው/ከጉናቸው በሚተኙ ሰዎች አካላዊ እና አእምሮአዊ ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል። ከፍተኛ ድምጽ ያለው ማንኮራፋት ኦብስትራክቲቭ ስሊፕ አፕኒያ ከሚባል የጤና ችግር ጋር ይያያዛል። ይህ የጤና ችግር የጉሮሮ ክፍል ግድግዳዎች እንዲፍታታ እና እንዲጠብ በማድረግ የተለመደ የመተንፈስ ሥርዓትን በማስተጓጎል የኦክስጅን እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል።
ኦብስትራክቲቭ ስሊፕ አፕኒያ የልብ የሥራ ማቆም ዕድልን በ140 ፐርሰንት ፣ በስትሮክ የመመታት ዕድልን 60 በመቶ እንዲሁም ለልብ ህመም የመጋለጥ ዕድልን 30 በመቶ እንደሚጨምር ጥናቶች ያመለክታሉ። በትዳር ውስጥ ያሉ ጥንዶችም በማንኮራፋት ምክንያት ክፍል ለይተው እስከመተኛት ሊደርሱ ይችላሉ።
ማንኮራፋትን ወይም ስሊፕ አፕኒያን ለማስቀረት ከሚረዱ አማራጮች መካከል ክብደት/ውፍረትን መቀነስ ፣ ሲጋራ ማጨስን ማቆም ፣ የአልኮል መጠን መቀነስ ፣ አተኛኘት እና ትራስ አጠቃቀምን ማስተካከል መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን አድርጎ ለውጥ ካልመጣ ግን ወደ ጤና ተቋማት ሔዶ ተገቢውን ህክምና ማግኘት ያስፈልጋል፡፡
