ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሰው ቅርንጫፍ ኩባንያው ያደረገውን ተጨማሪ የካፒታል ኢንቨስትመንት ተከትሎ፣ ሌሎች አብረውት ኢንቨስት ያደረጉ አጋሮቹ ያጡትን የ2.78 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ መልሰው የመግዛት መብታቸው የተጠበቀ መሆኑን አስታወቀ።
የቴሌኮም ኩባንያው እና ደቡብ አፍሪካዊው የእናት ኩባንያው ቮዳኮም ግሩፕ ‘ቮዳፋሚሊ ኢትዮጵያ ሆልዲንግ’ በተሰኘው የኢንቨስትመንት ተቋማቸው አማካኝነት፣ እስከ እኤአ መጋቢት 2026 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 21.3 ቢሊዮን የኬንያ ሺሊንግ የሚያወጣ የካፒታል ማሰባሰቢያ ጥሪ ላይ ብቻቸውን ተሳትፈዋል።
ይህንን የካፒታል ማሳደግ ጥሪ ሳፋሪኮም እና ቮዳኮም ብቻቸውን በመሸፈናቸው በኢትዮጵያው ኩባንያ ውስጥ የነበራቸውን ጥምር ድርሻ ከ57.41 በመቶ ወደ 60.19 በመቶ ከፍ ማድረግ ችለዋል።
ይህ እርምጃ እንደ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን ፣ ብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት ያሉትን ሌሎች አጋር ኩባንያዎች የነበራቸውን የባለቤትነት ድርሻ እንዲቀንስ አድርጎት ነበር።
ይሁን እንጂ ሳፋሪኮም አጋሮቹ የተዳከመውን ድርሻቸውን ወደነበረበት ለመመለስና ያጡትን የ2.78 በመቶ ድርሻ መልሰው መግዛት የሚችሉበት ሕጋዊ መብት እንዳላቸው በይፋ አረጋግጧል።
ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን የኔትወርክ ተደራሽነት ለማስፋፋት እና የንግድ እንቅስቃሴውን ለማጠናከር ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰ የሚገኝ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ እስከ መጋቢት 2027 ዓ.ም ድረስ ወጪና ገቢውን አጣጥሞ ሙሉ በሙሉ ትርፋማ መሆን እንደሚጀምር ግምቱን አስቀምጧል።
