የብሪክስ አባል ሀገራት የዶላርን የበላይነት ለመቀነስ እና እንደ ስዊፍት ያሉ ምዕራባውያን የሚቆጣጠሯቸውን የፋይናንስ መረቦች ለመተካት የሚያስችል አዲስ የዲጂታል ክፍያ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸው ተገለጠ።
ይህ አዲስ አሰራር በቅርቡ አባል የሆኑትን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትን የንግድ ልውውጥ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግራል ተብሎ ይጠበቃል።
በያዝነው የ2026 የፈረንጆቹ ዓመት በህንድ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ላይ በዋነኝነት የሚቀርበው ይህ እቅድ፣ ሀገራቱ የየራሳቸውን ብሔራዊ ዲጂታል ገንዘቦች (CBDCs) በቀጥታ እንዲያስተላልፉ የሚያስችል ነው።
ይህ አዲስ አሰራር በተለይም እንደ ህንድ ዲጂታል ሩፒ፣ የቻይና ዲጂታል ዩዋን እና የሩሲያ ዲጂታል ሩብል ያሉ ገንዘቦችን ያለ አሜሪካ ዶላር ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ለንግድ ልውውጥ ለማዋል የሚያስችል ሲሆን፣ ይህም የግብይት ወጪን ከመቀነሱም በላይ በምዕራባውያን የሚጣሉ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ስጋት በእጅጉ እንደሚቀንስ ተመልክቷል።
የህንድ ማዕከላዊ ባንክ ይህንን ጥያቄ ለጉባኤው አጀንዳነት ያቀረበ ሲሆን፣ አሰራሩ እንደ አንድ የጋራ ገንዘብ ሳይሆን እያንዳንዱ ሀገር የገንዘብ ሉዓላዊነቱን ጠብቆ የክፍያ መንገዱን ብቻ በጋራ እንዲጠቀም የሚያስችል ነው።
ይህ ጅምር በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የወርቅ ዋጋ በአንድ አውንስ ከ5,500 ዶላር በላይ በሆነ ፍጥነት መጨመር እና ለዶላር ያለው እምነት እየቀነሰ በመጣበት ወቅት መከሰቱ ለብሪክስ ሀገራት ትልቅ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተነግሯል።
ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ሲውል፣ እንደ ኢነርጂ እና ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች ያሉ ግዙፍ የንግድ ልውውጦች በአለም አቀፍ ቀውስ ወቅት እንኳን ሳይስተጓጎሉ እንዲቀጥሉ የሚያደርግ አማራጭ የፋይናንስ መስመር ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።
