ታላቁ ሊቅ አቡነ ጎርጎርዮስ ታሪካቸው በደማቅ ቀለም የተጻፈላቸው፣ ምኞታቸው የተተገበረላቸው፣ ርእያቸውን ማሳካት ያቻሉ የ20ኛ ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ኮከብ ናቸው፡፡
በርካታ የማኅበረ ቅዱሳን ልጆቻቸው ስለ ሊቁ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ስለ አቡነ ጎርጎርዮስ ታሪክ ሲናገር ስሰማው በጣም የሚመስጠኝ መምህር ሙሉጌታ ኃ/ማርያም ነው፡፡ እሱ ስለ ሊቀ ጳጳሱ ሲያወራ እኔም አብሬ የነበርኩ ያህል ነው የሚሰማኝ፡፡
ያሠለጠኗቸው ደቀ መዛሙርት ከሊቀ ጳጳሱ የተጋባባቸው ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ቅናት ይታይባቸዋል፡፡ በዘመኑ ለወንጌል ያሳዩት የነበረውን ቅናት ስንሰማ እግዚአብሔር በሊቀ ጳጳሱ የሠራውን ሥራ እናደንቃለን፡፡ ትውልዱም ሥራቸውንና ስማቸውን ጠብቆ አቆይቶላቸዋል፡፡
ሊቁ አቡነ ገብርኤልም ስለአቡነ ጎርጎርዮስ በሰፊው ተርከውልኛል ነበር፡፡ ከአቡነ ገብርኤል ጋር ይቀራረቡ ነበር፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስን ደርግ አስሯቸው ነበር፡፡ ወደ ዝዋይም የተላኩት በቅጣት መልክ ነበር ይባላል፡፡
ከፓትርያርክ አቡነ ተክለሃይማኖት ጋር ነገረ ሠሪዎች አጣልተዋቸው ነበር ብለውኛል፡፡ ደማቅ ታሪክ ሊሠሩበት ‘የሸዋ ሊቀ ጳጳስ’ ሆነው ወደ ዝዋይ አቀኑ፡፡ አሁን ዝዋይ ሐመረ ብርሃን ሲያስታውሱ ያለ አቡነ ጎርጎርዮስ ማሰብ አይቻልም፡፡
በ1980ቹ መጀመሪያ ቤተ ክርስቲያንን ከዐለማዊ ፈተና ለማውጣት የነበራቸውን አርቆ አሳቢነትና የሠሯቸው ሥራዎች ፍሬ አፍርተው ባይሆን ኖሮ ቤተ ክርስቲያንም አሁን ከገጠማትም በላይ ከፍተኛ ስደትና ጉስቁልና በደረሰባት ነበር፡፡ አቡነ ጎርጎርዮስ ሊወጋት የሚችለውን ‘የተማረ’ ትውልድ የሚወጋትን የሚከላከል (መካች) አድርገው ሠርተውታል፡፡
ባለፈው ዐመት ለንደን ላይ ገቢ ማሰባሰብ የተደረገላት የካሪቢያን ኦርቶዶክሳውያንን የሰበሰበችውን ቤተ ክርስቲያን አቡነ ጎርጎርዮስ ያቋቋሟት መሆኗን ሰምተናል፡፡ አሁን ያሉት የቤተ ክርስቲያኗ ካህናት ስለ ሊቀ ጳጳሱ ሲያነሡ በእንባ ነው፡፡ አብዛኞቹን ያኔ ዘዋይ ወስደው ያሠለጠኗቸው ናቸው፡፡
ሊቀ ጳጳሱ ተተኪ ጳጳስ አለማግኘታቸው ግን ሁሌም ያስገርመኛል፡፡ ከዚያ ይልቅ ‘ወጣቶቹ የአቡነ ጎርጎርዮስን ስም በተደጋጋሚ ያነሣሉ’ የሚሉና ሥራቸው መነገሩ የሚያበሳጫቸው ሊቃነ ጳጵሳት መኖራቸውን እንሰማለን፡፡
ታዲያ ከሊቀ ጳጳሱ አይረሴ ሥራዎች መካከል የታሪክ መጻሕፍት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዐለም መድረክ የሚታወቁ ሥራዎቻቸው ናቸው፡፡
ሁለቱን መጻሕፍት የሚመስሉ ሁለት ኮርሶች በቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ይሰጡ እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ EOTC Church history and World Church History. የEOTC Church history መምህሩ ግርማ ባቱ ሊቀ ጳጳሱን በተደጋጋሚ ይጠቅሳቸው እንደነበረም አስታውሳለሁ፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ስማቸው ሲጠቀስ ደስ ከሚሉኝ ሊቃውንት መካከል ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ሉሌ መላኩ፣ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ (የኋላው አቡነ መልከጼዴቅ) እና አቡነ ጎርጎርዮስ ናቸው፡፡ ሊቁ በጣት ከሚቆጠሩ የሀገራችን የታሪክ ተጠቃሾችም አንዱ ናቸው ማለት ነው፡፡
ሊቁ በአብነት ትምህርት፣ በነገረ መለኮት፣ በታሪክ፣ በአስተዳደር፣ መጻኢውን አርቆ በመመልከትም ጭምር ልዩ አባት ነበሩ ማለት ነው፡፡ አስገራሚ አባት፡፡
ታዲያ የእኒህን ታላቅ ሊቅ የታሪክ መጻሕፍት እነ ደብተራ በአማን የማርታት ሥራ ሠርተው፣ የሊቀ ጳጳሱንም ታሪክ ጨምረውበት፣ በዚህ መልክ አውጥተውታል፡፡ ይኸ ድንቅ አበርክቶት ነው፡፡ ደብተራ በአማን ‘ሚናችን እምብዛም ነው’ ብሎ ጽፎ አንብቤለሁ፡፡ ነገሩ የትኅትና ሆኖ ካልሆነ እንጂ ያደረጉት ነገር ትልቅ ነው፡፡
1) ሁለት የነበሩትን መጻሕፍት በአንድ ትልቅ መጽሐፍ ነው ያወጡት፣ ትልቅ ጉልበት ይጠይቃል፣
2) ከመጻሕፍቱ በተጨማሪ የሊቀ ጳጳሱን ታሪክም ጨምረውበታል፣ ይኸ ቀላል ድካምና ጥናት ሊሆን አይችልም፣
3) የግርጌ ማስታወሻ ጨምረውበታል፡፡ ይኸ ደግሞ ከፍተኛ የማርታት ሥራና ማብራሪያ ስለሆነ በጣም አድካሚ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
4) አርመውና አስተካክለው፣ ዘመኑን በሚዋጅ የሕትመት ደረጃ እንዳወጡት ሰምተናል፡፡
ይኸንን ሁሉ ስንሰማ ሥራው ቀላል ያልሆነ አስተዋጽኦ የታከለበት በቤታችን ልናስቀምጠውና ልንጠቀምበት የሚገባን ድንቅ ስጦታ መሆኑን እናምናለን፡፡
ለሥራው የደከማችሁ ሁሉ እናመሰግናለን ‼️
መልካም ንባብ!
