ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን ጨምሮ 18 ከፍተኛ የትግራይ የፖለቲካና የጦር መሪዎች፣ በፌደራል መንግሥት በተሾሙ 64 የጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ከጥቅምት 2013 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም ድረስ በነበረው የትግራይ ደም አፋሳሽ ጦርነት፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ሚያዝያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና ለጠቅላይ የምርመራ መምሪያ የቀረበው የጽሁፍ ክስ እንዳመለከተው፣ የተጠቀሱት ተከሳሾች በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል።
ክሱ የቀረበው አቶ አበራ ንጉስ በተባሉ የህግ ምሁርና ጠበቃ እንዲሁም ከጥቅምት እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም በፌደራል መንግስት በተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር የፍትህ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ባገለገሉ ግለሰብ መሆኑ ታውቋል፡፡
ቲክቫ ኢትዮጵያ ስለ ክስ ሂደቱ ያቀረበዉን ዘገባ ከዚህ በታች ቀርቧል
“ ‘እኛን በርሃ ሊያስቀሩን የሚችሉ ኃይሎች ሳይሆኑ ከወዲሁ በእንጪጩ መቀጨት አለባቸው፣ ባንዳዎች ናቸው’ የሚል ፕሮፓጋንዳ ከተሰራ በኋላ እርምጃ ተወስዷል ” – አቶ አበራ ንጉስ ስለ 63 ሰዎች ግድያ
“ ድርጊቱ ዝቅ ሲል የእድሜ ልክ እስራት ከፍ ሲል ደግሞ የሞት ፍርድ ቅጣት ያስቀጣል ! ”
ቲክቫህ ኢትዮጵያ እነ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር)፣ አቶ ጌታቸው ረዳና ሌሎች 18 ግለሰቦችን ጨምሮ ላቀረባችሁት የግድያ ወንጀል ማስረጃ አለ ? ሲል ከዚህ ቀደም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ለሰሩት፣ ጠበቃና የሕግ ባለሙያ አቶ አበራ ንጉስ ጥያቄ አቅርቧል።
ጠበቃና የሕግ ባለሙያው ምን መለሱ ?
“ የቀረበው የወንጀል መደበኛ ክስ ሳይሆን የጥቆማ ክስ ነው። ጥቆማ ይዞ ለመነሳት ወንጀሎች ከተፈጸሙ መፈጸማቸው በቂ ነው።
ግድያና ሌሎች ከባባድ ወንጀሎች ከተፈጸሙ ጥቆማ ለመስጠት በቂ ነው። ጥቆማ ሰጪ እንዲያውም ማስረጃ ላይጠበቅበት ይችላል። ምክንያቱም በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ትልቁ ሚና ወንጀለኞችን ለይቶ ለሕግ ማቅረብ የመንግስት ብቸኛ ሥራ ነው ” ብለዋል።
በርካታ አመራኖችና ሠራተኞች አስተዳደራዊ አገልግሎት እንዲሰጡበት በ2013 ዓ/ም በትግራይ ክልል ተቋቁሞ የነበረውን ጊዜያዊ አስተዳደሩንም ለክሱ መነሻ አድገዋል።
አቶ አበራ ስለድርጊቱ አክለው ምን አሉ ?
“ ሕወሓት በወቅቱ ከፌደራሉ መንግስት ጋር ባደረገው ጦርነት በርሃ መውረድ ብቻ ሳይሆን የተመረጠ መንግስትን ለመመለስ የትጥቅ ትግል/የሽምቅ ውጊያን ምርጫው አድርጎ በትግራይ ይንቀሳቀስ እንደነበር፤ በኋላም ሰኔ 21 ወደ መቀሌ እንደተመለሰ የሚታወቅ ሀቅ ነው።
በዚህ መሀል ላይ እኔ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ ሆኘ አገልግያለሁ። ሕወሓት ከበርሃ ገና ወደ መቐለ ሳይገባ ግድያዎች ይፈጸሙ እንደነበር የምናውቀው እውነታ ነው።
በክሱ ከቁጥር 1 እስከ 7 የተጠቀሱት በወቅቱ ለነበረው እንቅስቃሴ ‘ሴንተራል ኮማንድ’ ተብለው ወታዳራዊና ፓለቲካዊ ጉዳይ ሲመሩ የነበሩ ሰዎች ይህ ጊዜያዊ አስተዳደር የተመረጠ መንግስትን ተክቶ/ብልጽግናን ያደራጀው ኃይል የተገኙ ስለሆኑ፣ ብልጽግናም በወቅቱ ‘ጠላት’ ተብሎ ተፈርጆ ስለነበር ልክ በፍረጃው ደረጃ ‘ጠላት ናቸው’ ተብለው ተፈርጀዋል።
ፍረጃውን ተከትሎ ሴንራል ኮማንድ ጥር 21/ 2013 ዓ/ም የጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና ተግተው የሚሰሩ ከፓለቲካ ከሹመት ውጪ ያሉ የመንግስት ሠራተኞችን፥ ‘እኛን በርሃ ሊያስቀሩን የሚችሉ ኃይሎች ሳይሆኑ ከወዲሁ በእንጪጩ መቀጨት አለባቸው፣ ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው የሰጡ ባንዳዎች ናቸው’ የሚል ቅጥያ ስም ተሰጥቶ ፕሮፓጋንዳ ከተሰራ በኋላ እርምጃ ተወስዷል።
የወረዳና ዞን አስተዳዳሪዎች ሪፓርት ያደረጉልን ነበር። የ63 ሰዎች ግድያ፣ የአንድ ሰው የግድያ ሙከራ ድርጊት ዛሬ ቀረበ እንጂ ወደ 38ቱን ትግራይ እያለን የሰበሰብናቸው/ከየወረዳ የመጡልን ናቸው በወቅቱ።
ስለዚህ ግድያ ተፈጽሟል ምንም ጥያቄ የለውም። አስተዳደራዊ ሥራ ሲሰሩ የነበሩ፣ የፓርቲ ፓለቲካ አጀንዳ ያነገቡ አይደሉም።
በወቅቱ ሲደረግ በነበረው ጦርነትም ከፌደራል መንግስቱ ጋር ወግነው ወታደራዊ ሥራ ያልሰሩ ናቸው። የተገደሉት፥ በረድኤት፣ በሕክምና፣ ወይ አስተዳደራዊ ሥራ ሲሰሩ የነበሩ ብቻ እንደሆነ የሚታወቅ ሀቅ ነው” ብለዋል።
በሕጉ መሠረት በእንዲህ አይነት ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ለፍርድ ሲቀርቡ የምን ቅጣት ይጠዝቃቸዋል? ለሚለው ጥያቄም፣ “ድርጊቱ ዝቅ ሲል የእድሜ ልክ እስራት ከፍ ሲል ደግሞ የሞት ፍርድ ቅጣት ያስቀጣል ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
