የአሜሪካ የ2027 ዲቪ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲከፈት ተወሰነ

Date:

የአሜሪካ ፍርድ ቤት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለ2027 የተለያዩ ሀገራት ዜጎች የቋሚ መኖሪያ ፈቃድ ግሪን ካርድ የሚያገኙበትን የዳይቨርሲቲ ቪዛ (DV) ሎተሪ ፕሮግራም እንዲከፍት አዟል።

የዋሽንግተን ዲሲ የፌዴራል ዳኛ ጂንሱክ ኦህታ በጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ/ም ባሳለፉት ውሳኔ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮና ሚኒስቴሩ የ2027 የሎተሪ ምዝገባን እንዲከፍቱ አስገዳጅ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ውሳኔው የተላለፈው የአሜሪካ መንግሥት የ2027 የግሪን ካርድ ሎተሪ ምዝገባን በጊዜው ባለመክፈቱ፣ ፕሮግራሙ በተግባር ሊሰረዝ ይችላል በሚል ሬድ ኢግል ሎው የተባለ የሕግ ተቋም ክስ መስርቶ ነው። ተቋሙ የምዝገባ ጊዜ እንዲወሰን ባቀረበው ክስ ላይ የወሰነው ፍርድ ቤት ምዝገባው እንዲከፈት አዟል።

በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ፦

– የምዝገባ ዝርዝሮችን እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2019 ወይም October 29/2026 እንዲያሳውቅ፣

– ምዝገባውን ከጥቅምት 22/2019 ወይም November 1/2026 ጀምሮ ለ30 ቀናት እንዲከፍት

– የተመረጡ አመልካቾችን እስከ ህዳር 24/2019 ወይም December 3/2026 ድረስ እንዲያሳውቅ ተወስኗል።

ምንም እንኳን የፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ተግባር ላይ ውሎ ምዝገባው ቢከፈትም የተመረጡ አመልካቾች የቪዛ ሂደታቸው እስከ መስከረም 20/2020 ወይም መስከረም 30/2027 ድረስ መጠናቀቅ ስላለበት በምዝገባውና በቪዛ አሰጣጡ ሂደት ላይ በትራምፕ አስተዳደር የሚከሰት መዘግየት አንዳንድ አመልካቾች ቪዛ የማግኘት ዕድላቸውን ሊያሳጣ እንደሚችል ስጋት ተነስቷል።

የግሪን ካርድ ሎተሪ ዋና ዓላማው በየዓመቱ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር አነስተኛ ከሆነባቸው ሀገራት ለሚመጡ ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት ዕድል መስጠት ነው።

ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ በ1990 በወጣ የኢሚግሬሽን ሕግ የተቋቋመ ሲሆን በዓመት እስከ 55 ሺህ የሚደርሱ የቪዛ ዕድሎችን ይሰጣል።

ሆኖም ግን በሎተሪው መመረጥ ብቻውን ግሪን ካርድ ማግኘትን አያረጋግጥም ወይም ወደ አሜሪካ መሄድን አያረጋግጥም። አመልካቾች የተወሰነውን የትምህርት፣ የሥራ ልምድ ፣ የህግ መስፈርቶች እና ሌሎች የቪዛ ብቁነት ሁኔታዎችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።

የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ አቅርቧል። ይግባኙ በሚታይበት ወቅትም የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ታግዶ እንዲቆይ መጠየቁን ፎርብስ ዘግቧል።

@tikvahethiopia

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አለሁ እኔ ለወገኔ የድጋፍ ጥሪ

እሺ ምን እናድርግ? አርሲ ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊነት ወንጀል የሆነባቸው አካባቢዎች...

በኢትዮጵያ ከ1.6 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከፍተኛ የእይታ ችግር አለበት

በኢትዮጵያ ከ1.6 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕብረተሰብ ከፍተኛ የእይታ ችግር...

3ኛው የሩሲያ – አፍሪካ ጉባኤ በሞስኮ ይጀምራል

ጥቅምት 28 እና 29 እ.ኤ.አ.3ኛው የሩሲያ - አፍሪካ ጉባኤ...

ዳሸን ባንክ  “ዳሸን ኤር ፔይ” የተሰኘ  የክፍያ አገልግሎት አስተዋወቀ

  ዳሸን ባንክ ለንግድ ተቋማትና ለደንበኞች ግብይትን በተቀላጠፈ መልኩ ለማከናወን...