ይድረስ ለቅዱስ ሲኖዶስ
ጉዳዩ :- ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ መምሪያ እንዲኖር ስለመጠየቅ
- ይህ ሕፃን ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። ምናልባትም አፉን አልፈታም። በአንገቱ ላይ ያሰረው መስቀል ምን እንደሆነ እንኳን ትርጉሙን አያውቅም። ሃይማኖቱንም ዘሩንም ፖለቲካም ኢኮኖሚም አያውቅም
። የሚስበቅ የሚሮጥበትና የሚጫወበት እንጂ የሚማርበት የሚሠራበት ዕድሜ ላይ እንኳን አልደረሰም። ይህንን አይተን እንቅልፍ እንዴት በዓይናችን ይዞራል? እንዴትስ ልንረሳው እንችላለን? እኛ እንዲህ ከታመምን እዚህ ሕፃን ላይ ሰይፍ ያሳረፉ እንዴት ተኝተው ያድሩ ይሆን? የዚህ ሕፃን ኃጢአት ያልሠራች ነፍስ እግዚአብሔር ፊት ስትቆም ምን ብላ ታስፈርድ ይሆን? እሳት አይዘንብ ይሆን? ይህ ሕፃን በአርሲ ክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ምን ላይ እንደደረሰና ቢሳካላቸው ለእኛም የሚያስቡትን ጥጉን ማሳያ ነው። እንደዚህ ሕፃን ንጹሕ ብትሆኑም አይቀርላችሁም ነው። ምንም ብንል ይህን መልአክ የመሰለ ሕፃን አይቶ የማያዝን አካል ሊያዝንልን አይችልም።
አምና ልክ ይህን ጊዜ ተመሳሳይ ጥቃት ደረሰ። በበኩሌ በሶሻል ሚድያ በዚህ https://www.facebook.com/share/p/19mnnoAPQK/?mibextid=wwXIfr ማስፈንጠሪያ ላይ የምታነቡትን ጽሑፍ ጻፍሁ። ብዙዎችም የተሰማቸውን ኀዘንና ቁጭት በታያቸው መንገድ ገለጹ። ሆኖም ተጯጩኸን ምንም ያህል ለውጥ ሳይመጣ ተረሳ። መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለመቀየር ምንም ነገር ስለማንሠራ ‘ጮኸው ፣ ጮኸው ይተዉታል’ ከመባል በስተቀር ምንም አላተረፍንም። ገዳዮቻችን ግን አላማቸውን አልረሱትም አዘናግተው ደገሙት። ድጋሚ ሲከሰት ያንኑ ዓይነት ጽሑፍ ደግሞ መጻፍ ‘ተመሳሳይ ነገር እያደረጉ የተለየ ውጤት መጠበቅ’ እንደሆነ ታየኝ። እውነት ለመናገር ‘እገሌ ምነው ዝም አለ?’ ላለመባል የሚደረግ ማስመሰልም ሆኖ ታየኝ። እንደዛ ከማድረግ ደግሞ ከልብ የሆነ ጸሎትና ዝምታ ይሻላል።
የሚገርመው ‘አህያውን ፈርቶ ዳውላውን’ እንደሚባለውም ዋናውን ችግር ትተን እርስ በእርሳችን በመናከስና አንዱ ሌላውን በማጥቃትና ማሳጣት ላይ ብዙ ጊዜ አጠፋን። በገላ. 5፡15 ሐዋርያው ‘እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ’ እንዳለው እኛኑ በሚጎዳ መሰዳደብና መፈራረጅ ኃይላችንን ጨርሰን ቁጭ ስንል እነርሱ ግን አሁንም ሌላ ዙር ቀጠሉ። እንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ በጣም ተገማች (predictable) ስለሆኑ በተደጋገሙ ቁጥር ያተረፉልን ንቀት ብቻ ነበር።
በስልታዊ ዕቅድ (strategy) የሚደረግን ጥቃት ምንም ስልት በሌለው (non- strategic) መንገድ ለመፍታት ስለምንሞክርም ምንም ነገር መለወጥ አልቻልንም። በዚህ ምክንያት ከሌላው ቀድሞ በመጮህ ለቤተ ክርስቲያን የበለጠ አሳቢ መስሎ መታየትና ሌሎችን የማሳጣት መብት መጎናጸፍ እንደ ስኬት እየታየ መጣ። ሞትን ከማስቆም ይልቅ ‘ማን የበለጠ አለቀሰ?’ የሚለው የራስን ጽድቅ የማስመዝገብ (virtue signaling) እሽቅድድምና ‘እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ’ ዓይነት የማርታ ክስ አየሩን ይዞት ዋናው ጉዳይ ተዘነጋ። አሁንም እንደዚህ ሕፃን ያሉ ንጹሐን ከግፍ አላመለጡም።
በዚህ ዙር የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ግን በቀጥታ ሀገረ ስብከቱም ቅዱስ ሲኖዶስም ቀድመው ምላሽና መረጃ ስለሠጡ እንደዚሁም ከየአቅጣጫው ችግሩን የመተንተንና መፍትሔ የመጠቆም ዝንባሌዎች እየተበራከቱ ስለመጡ አሁን ድረስ በምልዓተ ጉባኤ ላይ ካለው ከቅዱስ ሲኖዶስ ምን ይጠበቃል? በሚለው ላይ የበኩሌን ሃሳብ ለማዋጣት ዕድል የሚሠጥ ሆኖ ታየኝ። ስለዚህ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ግድ ሆነብኝ። የምጽፈው ‘ብለን ነበር ሰሚ አጥተን ነው እንጂ’ ብሎ ቤተ ክርስቲያን ላይ ለመመጻደቅ ሳይሆን ውሳኔ ሰጪ አካላት ቢመለከቱት የሚያጤኗቸው ሃሳቦች ከተገኙ በሚል ነው።
ከቅዱስ ሲኖዶስ ምን እንጠብቃለን?
ቅዱስ ሲኖዶስ በተመሳሳይ ጥቃቶች ወቅት እስከ አሁን ያደረጋቸውን ምላሾች በዝርዝር እንመልከታቸው።
የሰማዕትነት ክብር ስም መሥጠት (ለሊብያ ሰማዕታት) ፣ ጸሎተ ምሕላና ፍትሐት ማድረግ ፣
ጥቃቱን በሀገረ ስብከት ደረጃ ፣ አለዚያም በቅዱስ ሲኖዶስ በማውገዝ መግለጫዎችን ማውጣት ፣ የመንግሥት አካላትን በግንባር ቀርቦ ማነጋገር ፣ ተጎጂዎቹን ወደ ሥፍራው ሔዶ ማጽናናት ፣ ማኅበራትንና ምእመናንን በማስተባበር ተፈናቃዮችን መደጎም ናቸው።
እነዚህ ምላሾች ቀስ በቀስ እየቀዘቀዙ የመጡ ሲሆን በተናጠል አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳት ለብቻቸው መግለጫ በማውጣት ፣ የተራድኦ ሥራ በመሥራት እንደ ሲኖዶስ ምላሽ ያልተሠጠበትን ሁኔታ በራሳቸው ለመወጣት የሞከሩባቸው ጊዜያትም ነበሩ። የተወሰዱት እርምጃዎች ግን ችግሩን በመፍታት ረገድ ያደረጉት አስተዋጽኦ ዝቅተኛ በመሆኑና ነገሮች ተባብሰው በመቀጠላቸው የነበሩት ምላሾችም ቀስ በቀስ ቀርተዋል። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶሱን ‘ለመንጋው የማይገደው’ እረኛ አድርጎ በማየት ተስፋ የቆረጠውና ከእንግዲህም ምንም የማይጠብቀው ሰው ቁጥር እንዲበዛ ምክንያት ሆኗል።
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመሩት በመንፈሳዊ ትምህርታቸው እና በገዳማዊ ሕይወታቸው ተመልምለው እንጂ ከጥቂቶች በስተቀር በአስተዳደር ዘርፍ በትምህርትና በሥራ ሲዘጋጁ ኖረው እንዳልሆነ ይታወቃል። በእርግጥ መንፈሳዊነት ከተኖረበት ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዳደር በቂውና ዋነኛው መሣሪያ ነው። የቤተ ክርስቲያን ችግርም የሚፈታው በጠረጴዛ ዙሪያ ከሚደረግ ውይይት በላይ በመንበሩ ዙሪያ በሚደረገው ቅዳሴ መሆኑ የታወቀ ነው። ቤተ ክርስቲያን ክፉ ዘመናትን የተሻገረችው በብልጣብልጥ አዋቂዎች ሳይሆን በየዋሃን መናኞች መንፈሳዊ ብልሃት እንደነበረ ታሪክ ያስታውሰናል።
ነገር ግን ሐዋርያው ‘ዘመኑን እየዋጃችሁ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ’ እንዳለው ሆኖም ያለንበት የቀበሮና የተኩላ ዘመን በመሆኑ በፍልጥ የመጣውን በፈሊጥ የማስተዳደር ጥበብን የሚጠይቅ ዘመን ነው። እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ፣ እነ ቅዱስ ጎርጎርዮስ እና እነ ቅዱስ ባስልዮስ ከባዱን ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ያሳለፏት የዘመኑን ጥበብ በመማራቸው እና የአስተዳደርም የንግግርም ጥበባቸው ዓለም ከነበራት የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ ስላልነበረ ነው። ሊቃነ ጳጳሳት በሰሞነኛነት ፣ በገዳም አበምኔትነት ፣ በደብር አለቅነት ፣ በሰባኬ ወንጌልነት ፣ በወረዳ ቤተ ክህነት ኃላፊነት ፣ በሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት የሥራ ልምድ አካብተው ፣ በሁሉም መዋቅር ውስጥ ሠርተው ተፈትነው ወደሚበልጠው ሲመት ሲደርሱ በቀላሉ ማስተዳደር የሚችሉ ይሆናሉ።
በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ አገላለጽ ‘ተቋማዊ እንክብካቤ ሳያገኙ’ ከባድ የኃላፊነት ሸክምን በአንድ ጊዜ የተረከቡ አባቶች ከሆኑ ግን ሸክሙ ይከብዳቸዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥቂት ዐሠርት ዓመታት በፊት ለጵጵስና ከመሾምዋ አስቀድማ ልጆችዋን ወደ ልዩ ልዩ ሀገራት ለከፍተኛ ትምህርት እየላከች ለዓመታት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ፣ የሌሎች ሀገራትን ልምድ እንዲቀስሙ ታደርግ ነበር።
በዚህም ምክንያት እንደ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ዓይነት ጳጳሳትና እንደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዓይነት ፓትርያርኮች ኖረዋት አስደናቂ አስተዳደራዊና መንፈሳዊ መሠረት ማስጣል ችላ ነበር። ይህ ዓይነቱ ልምድ አሁን አሁን ጨርሶ እየቀረ የመጣና ምናልባት መረጃ አጥሮኝ ካልሆነ በቀር ቤተ ክርስቲያን ‘እዚህ ሔደህ ተምረህልኝ ና’ ብላ ለነገ የምታዘጋጀው ሰውም የለም። ካሉትም አባቶች በዕድሜ ገና የሆኑ ብዙ መሥራት የሚችሉ አባቶችን ምን ዓይነት ድጋፍ ቢደረግላቸው የበለጠ መሥራት እንደሚችሉ ስላልታሰበበት አቅም እየባከነ እንዳለ ይታያል።
ይህ ሁኔታ የበለጠ ዋጋ የሚያስከፍለን ከውስጣዊ የአስተዳደር ክፍተታችን በላይ አሁን እየገጠመን ያለው ከውጪ የሚወረወር ጥቃት ሲመጣ ነው። እንደሚታወቀው ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓት የሚሰበሰበው በጥቅምትና በርክበ ካህናት ብቻ ነው። በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰበሰብ ጉባኤ በየወሩ የሚፈጸም ጥቃትንና በከፍተኛ ፍጥነት የሚደረግ ዘመቻን እንዴት ለማስቆም ይችላል? በዚያ ላይ በየስድስት ወሩ ተከማችተው የሚጠብቁ እጅግ ብዙ የየሀገረ ስብከቱ አጀንዳዎችን ፣ የአስተዳደር ጉዳዮችን ፣ ሀገራዊ ሁኔታዎችን ወዘተ ተመልክቶ ውሳኔ መሥጠት በራሱ እጅግ አድካሚ ሲሆን በዕድሜ አረጋውያን አባቶች በሚበዙበት ቅዱስ ሲኖዶስ ላይ የአጀንዳውን ብዛት ለተመለከተው እንኳንስ ተወያይቶ ለመወሰን ውይይቱን ለመስማት በራሱ እጅግ አድካሚ ሒደት መሆኑን መገመት አያዳግትም።
ይህ ሁኔታ በየሥፍራው የሚከሰቱ ጥቃቶችን ለማስቆም ቀርቶ በአግባቡ ለማዘን ራሱ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር አይደለም። ጥቃት የሚደርስባቸው አህጉረ ስብከቶችም ለቅዱስ ሲኖዶስ ከማመልከትና መልስ ከመጠባበቅ ያለፈ ምንም ለማድረግ ይቸገራሉ። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ምንም ቢያደርግ ተወቃሽ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ ሁኔታ ተፈጥሮአል። ቅዱስ ሲኖዶስ ዝም ቢል ‘ለምን ዝም አላችሁ?’ ፣ መግለጫ ቢሠጥ ‘የመግለጫ ጋጋታ ምን ያደርጋል?’ ፤ ከመንግሥት አካላት ጋር ቢነጋገር ‘የመንግሥት ተላላኪ ናችሁ’ ፤ እርዳታ ቢሠጥ ‘ሕዝቡ ሰላም እንጂ መች ገንዘብ ቸገረው?’ ከመባል አያመልጥም። የዚህ ሁሉ መንሥኤ ግን ጉዳዩ በአግባቡ የሚያዝበት አግባብ አለመፈጠሩ ነው። ይህንን ሁሉ ችግር የዘረዘርሁት እንደ መፍትሔ ላቀርብ ላሰብሁት ሃሳብ እንደ መንደርደሪያ እንዲሆን ነው።
ቤተ ክርስቲያኒቱ ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ የሰላምና ደህንነት መምሪያ ያስፈልጋታል!! (ምናልባት ያለ ከሆነም እሰየው)
ቅዱስ ሲኖዶስ ለግንቦት ቀጠሮ ይዞ አበው ወደየሀገረ ስብከታቸው ሳይበተኑ በፊት ከጥቅምት እስከ ግንቦት ድረስ ለሚከሰቱ ተመሳሳይ ጥቃቶች እልባት እንዲተዉ እንመኛለን:: ይህም ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ የሰላምና ደህንነት መምሪያ ነው:: (ስያሜው ምንም ሊሆን ይችላል) ይህ መምሪያ በየሥፍራው የሚከሰቱ ጥቃቶች ዙሪያ የሚሠራ ፣ የአደጋ ስጋቶችን አስቀድሞ የሚያጠናና የሚተነትን ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን ሳይጠባበቅ የቤተ ክርስቲያኒቱንና የምእመናንን ደህንነት የሚከታተል ቢሆን ነገሩ የአንድ ሰሞን ጫጫታ ሆኖ ከመረሳት እንዲድን የሚያደርግ ሲሆን ቢያንስ ሙሉ ሥራውና ትኩረቱ ምእመናንና ካህናትን እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅርስ ደህንነት የሚያስጠብቅ ይሆናል። የቤተ ክርስቲያኒቱን የጥበቃ መዋቅርም ሁሉ የሚቃኝ ፣ ከመንግሥት የሰላም ተቅዋማት ጋር በትይዩነት የሚሠራ ሊሆን ይችላል::
ይህንን ሥራ የሚሠራው አካል ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ሆኖ ወይንም በሊቀ ጳጳስ እየተመራ በውስጡ በሀገርም ውስጥ ከሀገርም ውጪ ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሕግ ባለሙያዎች ፣ የሕዝብ ግንኙነትና ሚድያ ኤክስፐርቶች ፣ ቤተ ክርስቲያናቸውን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ልምድ ያላቸው የዲፕሎማሲና የደህንነት ባለሙያዎች ፣ የአይቲ ባለሙያዎች ፣ በሰብአዊ መብት ላይ የሠሩ ሰዎች ቢካተቱበትና ቤተ ክርስቲያን ልጆችዋን በአግባቡ መጠቀም ብትችል ማንም እየተነሣ የፈለገውን ሲያደርግ አቅም እንደሌላት መስላ ከመታየት ትድናለች። ሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናት በጸጥታና በደህንነት ዘርፍ ላይ ያላቸውን ልምድ መቃኘትም የሥራው አንድ አካል ሊሆን ይችላል።
ከዚያ ውጪ ወደድንም ጠላንም ቤተ ክርስቲያንዋ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆንዋ በብስጭትም ቢሆን ቅዱስ ሲኖዶስን ከማጥቃት መቆጠብ የሚጠቅመው ራሳችንን ነው። በእርግጥ ያለነው የምጽአት ዋዜማ ላይ እንደመሆኑ ብዙ የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች መታየት ከጀመሩ ቆይተዋል። የመጨረሻው ዘመን አንዱ ምልክት ቅትለተ ዘካርያስ (የካህናት መxደል) ነው። ይህ ደግሞ የሚጀምረው ከሰይፍ ሳይሆን ከሰብእና ገደላ (character assasination) ነው። ያለንበት ዘመን ደግሞ ምንኩስናንና ክህነትን የሚያዋርድ ብዙ ነገር በአደባባይ እየታየና እየተሰማ መሆኑን ሰይጣን በአግባቡ እየተጠቀመና ከክህነት ውጪ ንስሐም ቁርባንም ድኅነትም የሌለውን ክርስትና ሰው አልባ ለማድረግ እየተጣደፈ ነው።
ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ በቀኖና አለመከበር ምክንያት የቤተ ክርስቲያንዋን መሪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስንና ሊቃነ ጳጳሳትን ግርማ የሚገፍፍ ነገር ከውስጥም ከውጪም መብዛቱ ነው። የከፋው አደጋ ደግሞ በማኅበራዊ ሚድያ አንዱን አባት ወክለው ሌላውን እየሰደቡና ጉድ አወጣለሁ እያሉ በሊቃነ ጳጳሳት መካከል ጠብ የሚያጋግሉ የፌስቡክ አቡነ ቀሲሶች መፈጠራቸው ደግሞ ተቋማዊ ራስን ማጥፋት (institutional sucide) እየተፈጸመ እንዳለ የሚያሳይ ነው። የራሳችንን ቅዱስ ሲኖዶስ ባቃለልንና ውስጣዊ ችግሮቻችንን አደባባይ ባሠጣን ቁጥር እግዚአብሔር ከሚቀጣን ውጪ የሲኖዶሱን ከማንኛውም አካል ጋር የመደራደር አቅም በገዛ እጃችን እያዳከምንና ቤተ ክርስቲያንዋም ‘ሕዝባዊ መሠረት የሌላት’ ጥርስ አልባ ተቋም መስላ እንድትታይ መንገድ እየጠረግን ነው።
‘ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም’ እንዲሉ እኛ ከፍ ዝቅ አድርገን የሸኘናቸውን አባቶች ሌሎች ሽር ጉድ ብለው ሊያስተናግዷቸው አይችሉም።
እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ሲፈጸሙ በጉዳዩ ላይ ቢስማማም ባይስማማም ፣ እጁ ቢኖርም ባይኖርም መንግሥት ተጠያቂ መሆኑ የማይቀር ነው። ምክንያቱም ሕዝብ ደህንነቴ ተነካ ብሎ ሊጠይቀው የሚችለው ከመንግሥት ሌላ የበላይ አካል ስለሌለ ነው። በሥልጣን ላይ ያለን መንግሥት የሚደግፉትም የሚቃወሙትም ዜጎች እስከሆኑ ድረስ እኩል መብቴን አስከብርልኝ ብለው የመጠየቅ ፣ ለምን አላስከበርክም ብለው የመውቀስ መብት አላቸው። ስለዚህ ተጠያቂነቱ የሚመነጨው ከመንግሥትነት ነው። ሁሉም የየራሱ ድርሻ ቢኖረውም በቤተ ክርስቲያንና በልጆችዋ ላይ የሚደርስን ጥቃት ማስቆም ከመንግሥት አቅም በላይ ሊሆን አይችልም።
በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ሌላ ዓላማ የሚያስፈጽሙና ግፉ እንዲቀጥል የሚሠሩ አካላት ሁሌም ሊኖሩ ይችላሉ ፣ የዚያንኑ ያህል ደግሞ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑ ያም ባይሆን ለሕሊናቸው የሚታመኑ ይህ ዓይነቱ ግፍ እንዳይፈጸም የሚፈልጉ አካላትም አሉ። ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስና ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትወክለው አካል በአግባቡ ሥራውን ከሠራ በመንግሥት ወገን ሊደረግ የሚገባው እርምጃ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ይቻላል።
በተረፈ ግን ተስፋ አትቁረጡ:: ለፈጣሪ እንዲህ በሉት:-
“መምህር ሆይ፥ ስንጠፋ አይገድህምን?” ማርቆስ 4:38
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 16 2019 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
“ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” ኤፌ. 4:29-31
