የአንጋፋው ጋዜጠኛ ከበደ ሕይወትና ሥራን የሚዳስሰው መጽሐፍ ለንባብ በቃ

Date:


በአንጋፋው ጋዜጠኛ ከበደ አኒሣ ሕይወትና ሥራዎቹ ላይ የሚያተኩረውና “ኢትዮጽያ ትቅደም:- የከበደ አኒሣ ዱካዎች” የሚል ርእስ ያለው መጽሐፍ በዛሬው እለት ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።

“ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን ታሪካዊ መፈክር የፈጠሩትና ለሕዝብ ያስተዋወቁት ጋዜጠኛ ከበደ አኒሣ፤ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ፈር ቀዳጅ ከሆኑት መካከል አንዱ እንደነበሩም በመጽሐፉ ምረቃ ላይ ተገልጿል።

በ1924 ዓ/ም በቀድሞው አጠራር ወለጋ ጠቅላይ ግዛት ነቀምት ከተማ የተወለዱት አቶ ከበደ አኒሣ፤ ከመምህርነት አንስቶ እስከ ጠቅላይ ግዛት ሹመኝነት እንዲሁም ከሪፖርተርነት እስከ ፕሬስ መምሪያ አማካሪነት በድምሩ ለ37 ዓመታት ሀገራቸውን አገልግለዋል።

በጋዜጠኝነት ሙያቸው በ”የኢትዮጵያ ድምጽ” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጦች በዋና አዘጋጅነት፣ በ”የአሜሪካን ድምጽ” በሪፖርተርነት እንዲሁም በ”ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ” ጋዜጣ በጸሐፊነት ላይ መሥራታቸው ተገልጿል።

የማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ የሀገር አስተዳደር ሚኒስቴር፣ የሕዝባዊ ኑሮ እድገትና ዘመቻ መምሪያ እና ሌሎችም ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉባቸው ተቋማት ናቸው።

ጋዜጠኛ ከበደ አኒሣ መስከረም 2014 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን፤ በእሳቸው ሕይወትና ሥራዎች ላይ ትኩረቱን የሚያደርገው መጽሐፍ ቤተሰቦቻቸው፣ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቻቸው እና ወዳጆቻችው በማነጋገር እንዲሁም ከተለያዩ የሚድያ ተቋማት ጋር ያደረጓቸው ቃለ-መጠይቆችን ዋቢ በማድረግ የተጻፈ ነው።

የከበደ አኒሣ ሁለተኛ ልጅ የሆኑት አርቲስት መሠረተ-አብ ከበደ እንደተናገሩት፣ መጽሐፉ በዋናነት አቶ ከበደ በሦስት የአገዛዝ ሥርዓቶች ውስጥ የዘለቀው የሙያ አገልግሎታቸውን የሚቃኝ ነው።

መጽሐፉ የተዘጋጀበት ዋነኛ ዓላማም ከዐበይት ሀገራዊ ክስተቶች ጋር የሚቆራኘው የአቶ ከበደ ሕይወት ለመጪው ትውልድ መማሪያ ለማድረግ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የ”ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ” ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ የሆኑት አቶ ዓለም ኃይሉ በመድረኩ ላይ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ ከጋዜጠኛ ከበደ ጋር በቅርበት ከመተዋወቅ አልፈው ወዳጅ እንደነበሩ ተናግረዋል።

አቶ ከበደ ለሙያቸውና ለጋዜጣ ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ “ስሞት በጋዜጣ ገንዙኝ” ይሉ እንደነበርም አቶ ዓለም አስታውሰዋል።

የጋዜጠኛ ከበደ አንባቢነት በሥራቸው ላይ ይንጸባረቅ እንደነበር የገለጹት አቶ ዓለም፤ የሚጽፏቸው ርእሰ-አንቀጾች አጫጭርና ቀለል ያሉ ከመሆናቸው በተጨማሪም ከወቅቱ የቀደሙ እንደነበርም አስረድተዋል።

በአቶ ሰለሞን ዋስይሁን የተጻፈውና በጋዜጠኛ ከበደ አኒሳ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ትኩረቱን የሚያደርገው መጽሐፉ በዐሥራ አመስት ምእራፎች የተከፋፈለ ሲሆን፤ የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮችን ይዳስሳል።

መጽሐፉ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ የአቶ ከበደ ቤተሰቦች፣ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦች፣ ወዳጆች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል።

ጋዜጣ_ፕላስ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ሴቶችን በቤት ውስጥ በማገዝ  መልካም ማህበረሰብ መፍጠር ተጀምሯል

በቤት ውስጥ የሚሠሩ ተግባራትን ተከፋፍሎ በመሥራት ሴቶችና እናቶችን መደገፍ...

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...

ፈረንሳይ የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምታለች

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የኃይል...