የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የትንተና አቅምን ለማጠናከር እና በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔዎችን ለመደገፍ፣ ሁለት ገለልተኛ አባላትን የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አባል አድርጎ መሾሙን አስታወቀ።
ባንኩ ረቡዕ የካቲት 11 2018 ዓ.ም ባወጣዉ መግለጫ፣ ሹመቶቹ በብሔራዊ ባንክ ገዢ የቀረቡና በዳይሬክተሮች ቦርድ መጽደቃሸውን ግልጿል። ይህም በቅርቡ በተሻሻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ መሠረት የተከናወነ መሆኑን ገልጿል።
ባንኩ የውጭ አባላትን ማካተቱ የኮሚቴውን የሙያ ብቃት ለማሳደግ እና በቂ መረጃ ያላቸው የፖሊሲ ውይይቶችን ለማድረግ መሆኑን አመልክቷል።
እንደ መግለጫው ከሆነ፣ ተሿሚዎቹ በማክሮ ኢኮኖሚ ትንተና እና ፖሊሲ ዙሪያ ጠንካራ የትምህርት ዝግጅት እና የላቀ የሙያ ልምድ ያላቸው ምሁራን ናቸው።
በተጨማሪም፤ የባለሙያዎቹ ተሳትፎ በኮሚቴው ውስጥ ጥብቅ የሆኑ ውይይቶች እንዲደረጉ እና የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው የተጣለበትን ኃላፊነት ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲወጣ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።
ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ ሰፊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አካል የሆነውን የዋጋ መረጋጋትን የማስቀጠል እና የፋይናንስ ተቋማት በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን የማረጋገጥ ቁርጠኝነቱን በድጋሚ አረጋግጧል።
