በማዕከላዊ የአፍሪካ ክፍል የምትገኘው ጋቦን መገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የማኅበራዊ ሚዲያዎችን በአገሪቱ ውስጥ ግጭትን እያባባሱ እና መከፋፈልን እያሰፉ ነው በሚል ላልተወሰነ ጊዜ አገደ።
ማክሰኞ ምሽት በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የአገሪቱ ከፍተኛ ኮሚዩኒኬሽን ባለሥልጣን “ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት”፤ “የኦንላይን ዘለፋ” እንዲሁም “ያለፈቃድ የግል መረጃን ማሠራጨት” ለውሳኔዎቹ ምክንያት መሆናቸውን ገልጿል።
የባለሥልጣኑ ቃል አቀባይ ዤን ክላውዴ ሜንዶሜ የትኛው የማኅበራዊ ሚዲያ በዚህ ውሳኔ እርምጃ እንደሚወሰድበት ግልጽ ባያደርጉም በአገሪቱ ውስጥ ግን ዋትስአፕ፣ ቲክ ቶክ እና ፌስ ቡክ ዝነኛ ናቸው።
አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት የሚያስተዳድሩት ጄነራል ብሪስ ኦሊጉኢ ንጉማ እአአ በ2023 ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ካካሄዱ በኋላ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸንፈዋል።
የ50 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ከመምህራኖች እና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
ረቡዕ ዕለት ረፋዱ ላይ ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ መቋረጣቸውን ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።
ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ከሆነ የተወሰኑ ተጠቃሚዎች ፌስቡክ እና ቲክቶክን መጠቀም አልቻሉም።
ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት ጋቦን ማኅበራዊ ሚዲያዎች በወጣቱ ዘንድ ለመዝናኛም ሆነ ለሥራ ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው።
በዋና ከተማዋ ሊብራቪሌ የሚኖር ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የምግብ ቤት ባለቤት ንግዱን የሚያስተዋውቅባቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች መታገዳቸው ሥራው ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥርበት ተናግሯል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
