እየተገባደደ በሚገኜው የውሮፓውያኑ 2025 ዓመት የኢትዮጵያ ብር ከዓለማችን እጅግ ደካማ ገንዘቦች መካከል አንዱ ሆኖ መመዝገቡ ተገለጸ።
በየጊዜው እያሽቆለቆለ ለመጣው የኢትዮጵያ ብር መዳከም በርካታ መንስኤዎች ቢኖሩም ዋነኛው ግን የኢኮኖሚው አለመረጋጋት መሆኑንም “ኤክስኤስ.ኮም” የተባለ የምጣኔ ሀብት ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው መረጃ አመላክቷል።
በተቋሙ መረጃ መሠረት በዓመቱ ከዓለማችን እጅግ ደካማ ገንዘብ ካላቸው ሀገራት መካከል ኢራን ሊባኖስን እና ዚምባብዌን አስከትላ የአንደኝነቱን ደረጃ የያዘች ሲሆን ኢትዮዸያ ደግሞ ከየመን ቀጥሎ ከሀይቲ ደግሞ ተሽላ በ26ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የኢትዮጵያ ብር ባለፈው የጎርጎሪዮሱ ዓመትም ከሰሐራ በታች ካሉ ደካማ ገንዘብ ካላቸው አገራት ተርታ እንደሚመደብ የዓለም ባንክ ባወጣው መረጃ መግለጹ ይታወሳል።
መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እና ከብር መዳከም ጋር ተያያዘ የሚከሰተውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ የተለያዩ ፖሊሲዎችን እና መመሪያዎችን እየተገበረ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይሰማል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን በመከተል የዋጋ ግሽበቱን ለማርገብና ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፉን በቅርቡ አራተኛ ጉባኤውን ባከናወነበት ወቅት መግለቱም አይዘነጋም።
(#አዲስ_ማለዳ)
