የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ተሰጥቶ የነበረውን ወደ ቻይና ለሚላኩ የውጭ ንግድ ምርቶች የወጪ ንግድ ፈቃድ የመስጠት ብቸኛ ስልጣን በይፋ አንስቷል።
ከግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው በዚህ አዲስ ውሳኔ መሠረት፣ ሁሉም ፈቃድ ያላቸው የግልና የመንግስት የንግድ ባንኮች ወደ ቻይና ገበያ ለሚላኩ ምርቶች የወጪ ንግድ ፈቃድ የመስጠት፣ የሰነድ ክሬዲቶችን የመደገፍና ተያያዥ የባንክ አገልግሎቶችን የመስጠት ሙሉ መብት ተሰጥቷቸዋል።
ይህ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል በነበረው አጠቃላይ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ትብብር ስምምነት ምክንያት ተጥሎ የነበረው ገደብ፣ ማንኛውም ወደ ቻይና የሚላክ ምርት በንግድ ባንክ በኩል ብቻ እንዲያልፍ ያስገድድ ነበር።
ብሔራዊ ባንክ ይህንን አሰራር የቀየረው የውጭ ንግድ ዘርፉን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ፣ በባንኮች መካከል ጤናማ ውድድርን ለመፍጠርና ለላኪዎች ምቹና ተደራሽ የሆነ አሰራርን ለመዘርጋት በማሰብ እንደሆነ ገልጿል።
በመሆኑም ላኪዎች ከአሁን በኋላ የሀገሪቱ ትልቅ የንግድ አጋር ወደሆነችው ቻይና ለሚልኳቸው ምርቶች የመረጡትን የንግድ ባንክ በመቅረብ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ።
ይህ ታሪካዊ የተባለለት የፖሊሲ ለውጥ ከዚህ ቀደም በንግድ ባንክ ላይ ብቻ ይፈጠር የነበረውን የስራ መደራረብና የእንግልት አሰራር በእጅጉ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ላኪዎች ሰፊ የባንክ አማራጮችን እንዲያገኙ በማድረግ የግብይት ወጪን ለመቀነስ፣ የሰነድ ማረጋገጫ ሂደትን ለማፋጠንና አጠቃላይ የወጪ ንግድ ዘርፉን ለማሳደግ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ብሔራዊ ባንክ ሁሉም ባንኮች አዲሱን መመሪያ ተከትለው አሁን ባሉት የውጭ ምንዛሬና የወጪ ንግድ ደንቦች መሠረት አገልግሎቱን በአስቸኳይ እንዲጀምሩ መመሪያ አስተላልፏል።
