የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣው ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ፀደቀ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ ባደረገው ውይይት፣ ይህ አዲስ አሠራር የዜጎችን የመሬት ይዞታ የማግኘትና የመጠቀም መብት በማያጣብብ መልኩ ለውጭ ዜጎች ህጋዊ መሠረት መዘርጋቱ ለሀገሪቱ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት አጽንኦት ሰጥቷል።
ከእነዚህም ጥቅሞች መካከል የውጭ ካፒታል ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ማበረታታት፣ የቤት ልማትና ተደራሽነትን ማነቃቃት፣ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ሚዛናዊ ማድረግ እንዲሁም ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይጠቀሳሉ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይህን ረቂቅ አዋጅ አፅድቆ ወደ ተግባር ሲገባ የውጭ ኢንቨስትመንትን በማሳደግና የሪል ስቴት ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
