የዶይቼ ቬለ የአማርኛው ክፍል የመንግሥታት መለዋወጥ ሳይበግረው መረጃን ለአድማጮቹ እያደረሰ የዘለቀ የራዲዮ ጣቢያ መሆኑን የዶቼ ቬለ የአፍሪካ ክፍል ሀላፊ ክላውስ ሽቴከር ገለፁ።
ሃላፊው የጣቢያውን 60ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተደረገ ልዩ የክብረ በዓል ድግስ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት፤ የዶይቼ ቬለ የአማርኛው ክፍል የመንግሥታት መለዋወጥ፣ የፀጥታ ችግር እና ሌሎች ፈተናዎች ሳይበግሩት መረጃዎችን ለኢትዮጵያውን አድማጮቹ እያደረሰ ዛሬም አለ። ለዚህም የጣቢያው ተግባር እውቅና እና ከበሬታ እንደሚሰጡ ሀላፊው አመልክተዋል። ለወደፊቱም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በራዲዮ የተጀመረው አገልግሎት በጊዜ ሂደት ከተፈጠሩ የቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር ራሱን እያስማማ ዛሬ በድረ-ገጽ እና እንደ ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ቴሌግራም በመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለተከታታዮች እያቀረበ ይገኛል ያሉት ሀላፊው፤ በዚህ የቴክኖሎጂ ለውጥ ከተደረገው ሽግግር ጋር ራሱን በማስማማቱ የጣቢያውን ኤዲቶሪያል አመስግነዋል።
የዶይቼ ቬለ የአማርኛ አገልግሎት ለኢትዮጵያና ለአካባቢዉ ሃገራት ማሰራጨት የጀመረዉ መጋቢት 6 ቀን 1957 ነበር። ጣቢያዉ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ እና የዓለምን ዐበይት ጉዳዮች በዜና እና በትንታኔ እያቀረበ ስድስት አስርት ዓመታትን ከአድማጮቹ ጋር ዘልቋል።
ዶይቼ ቬለ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት የተጀመረበትን 60ኛ ዓመት አስመልክቶ በተዘጋጀው ልዩ ድግስ የዶይቼ ቬለ ኃላፊዎች፣ የአማርኛ ቋንቋ ክፍል የወቅቱ እና የቀድሞ ጋዜጠኞች እንዲሁም ዶቼ ቬለ የሚያሰራጭባቸው የልዩ ልዩ ቋንቋ ክፍል ባልደረቦችም ተገኝተው የበዓሉ ተካፋዮች ሆነዋል።
