በኢትዮጵያ ካለው የሕዝብ ቁጥር አንጻር በዘርፉ የሰለጠኑ እና በቂ እውቀት ያላቸው የጋብቻ አማካሪዎች ቁጥር ውስን ስለመሆኑ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሞያዎች ገልጸዋል፡፡
የማህበራዊ እሴትን ከማስጠበቅ እና ከፍተኛ ሚና ያለውን የቤተሰብ ተቋም አጽንቶ ለማስቀጠል በቀዳሚነት ቤተሰብ ሲመሰረት የቅድመ ትዳር የምክክር ሂደት አስፈላጊ ቢሆንም፤ እንደ ሀገር የጋብቻ ምክር በብዛት እንደማይስተዋል ተነግሯል፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ጥናት ባለሞያው አቶ መላኩ ጌታቸው እንደተናገሩት፤ ቤተሰብ ከልጅነት እድሜ ክልል ጀምሮ ከማህበረሰብ ጋር አብሮ ለመኖር የሚያስችል ስንቅ የሚያሲዝ እና ማህበራዊ መስተጋብርን የመፍጠር አቅም ያለው ተቋም ነው፡፡
“በጤናማ ቤተሰብ የተቀረጸ ማንነት በማበራዊ ሕይወት ላይ የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር አስቻይ ሁኔትን ለመፍጠር ያስችላል” ያሉት ባለሞያው፤ ማህበራዊ እሴትን ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይናገራሉ፡፡
ጤናማ ቤተሰብ መመስረት ለልጆች ከሚያስገኘው አውንታዊ አስተዋጾ በተጨማሪ ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ስለመሆኑ የተናገሩት ደግሞ፤ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ፕሮፌሰር በዕውነቱ ዘውዴ ናቸው፡፡
አክለውም የጋብቻ ምክክር የሚሰጡ ቢኖሩም በቂ ዝግጅት እና ልምድ ያላቸው የጋብቻ አማካሪዎች ዝቅተኛ ስለመሆኑ የገለጹ ሲሆን፤ ይህ በመሆኑም ቤተሰብን እንዴት መምራት እንደሚቻል በቂ ግንዛቤ ሳይያዝ ወደ ጋብቻ እንዲገባ እንደሚዳርግ ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት ትዳሩ አደጋ ላይ እንዲወድቅ እንደ ምክንያት የሚነሳ ጉዳይ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
በሰለጠው ዓለም ቅድም እና ድህረ ጋብቻ የምክክር ሂደት እንደ ሀገር እንብዛም ባይለመድም መሻሻሎች እንደሚተዋሉ ተነግሯል፡፡
አለመግባባቶች በቤተሰብ መሃል ሲፈጠር እንዴት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል እና የቤተሰብን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ ሃሳቦችን ለመረዳት የጋብቻ የማማከር አገልግሎት አስፈላጊነቱም አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡
(አሐዱ ሬድዮ)
