የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ
ቡድን ተጫዋች አለልኝ አዘነ ግድያ «ጥፋተኛ»’ ያላቸውን ሁለት ግለሰቦች በ16 እና 15 ዓመት ጽኑ እሥራት ቀጣ።
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹላይ ቅጣቱን የወሰነው ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ በዋለው ችሎት ነው። ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ሊጥል የቻለው ተካሳሾቹ መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት የ26 ዓመት ወጣት የሆነውን አለልኝ አዘነን አርባ ምንጭ ከተማ ውስጥ በመግደልና ራሱን ያጠፋ እንዲመስል በማድረግየግድያ ወንጀል በመፈፀማቸው ነው ተብሏል።
በወንጀሉ የተጠረጠሩ 1ኛ ተከሳሽና የሟች አለልኝ አዘነ ባለቤት ወ/ሮ
አደይ ጌታቸውን እና 2ኛ ተከሳሽ ሉንጎ ሉቃስን በፍርድ ችሎት ሲያከራክር መቆየቱን ለዶቼ ቬለ የገለጹት የጋሞ ዞን ፍትህ መምሪያኃላፊ አቶ ጤናው ጨርቆስ «የተከሳሾቹ ድርጊት በሰውና በሠነድ ማስረጃዎች በመረጋገጡ የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል።
በውሳኔው መሠረትም 1ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ አደይ ጌታቸው ላይ የ16 ዓመት እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ሉንጎ ሉቃስላይ 15 ዓመት ፅኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል» ብለዋል።
መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም አርባ ምንጭ ከተማ ውስጥ በሰው እጅ ሕይወቱ አልፏል የተባለው አለልኝ አዘነ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን እና ለባሕር ዳር ከነማ ተሰልፎ በመጫወት እንደሚታወቅ ከሀዋሳሸዋንግዛው ወጋየሁ የላከልን ዜና ያመለክታል።
DW Amharic
