ከአንድ ዓመት በፊት መካሄድ የጀመረው የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግሥት እድሳት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉን ተከትሎ፤ ቅርሱን ለመጎብኘት ወደ ከተማዋ የገቡ ከ56 ሺሕ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እና 1 ሺሕ 914 የሚሆኑ የውጭ ቱሪስቶች ቅርሱን መጎብኘታቸውን የጎንደር ከተማ የቅርስ ጥበቃ ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።
ቅርሱ ከ1980 ጀምሮ ምንም እድሳት እና ጥገና ሳይደረግለት ቆይቶ ባሳለፍነው ዓመት ጥገናው መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን፤ እድሳቱ ሦስት አይነት ሥራዎችን ያካተተ ስለመሆኑ የጎንደር ከተማ የቅርስ ጥበቃ ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ዓይቼው አዲስ ተናግረዋል።
ይህም እድሳት የመጀመሪው ሙሉ ጥገና፣ ሁለተኛው ግቢውን ማስዋብ እና ሦስተኛው የኤሌትሪክ ኃይል የመስመር ዝርጋታን ያካተተ መሆኑም ጠቁመዋል፡፡
በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ፋሲለደስ እንደተቆረቆረች በሚነገርላት ጎንደር ከተማ የሚገኘው እና ከ40 ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ተብሎ የተመዘገበው የፋሲል ቤተ-መንግሥት የቅርስ ጥበቃ እና እድሳት ሂደትን በተከተለ መንገድ መታደሱንም ቡድን መሪው ለአሐዱ አብራርተዋል።
እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፤ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተካሄደው የቅርሱ እድሳት ተጠናቆ ጎብኚዎችን ማስተናገድ ከጀመረ ወዲህ ከተማዋን ለመጎብኘት የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ቁጥር ከሌሎች ጊዜያት አንፃር በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።
አክለውም፤ እድሜ ጠገቡ የፋሲል ቤተ-መንግሥት እድሳት መጠናቀቁ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ማዕከል ከሆኑት እድሜ ጠገብ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው ጎንደር ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ልዩ ድምቀት ሰጥቶት ማለፉን አስታውሰዋል።
“በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ እያንሰራራ ይገኛል” ሲሉም አቶ ዓይቼው ተናግረዋል፡፡
የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት ፋሲል ግቢ በ1628 ዓ.ም. የተሠራ ሲሆን፤ በውስጡ ቤተ መዛግብት፣ የአፄ ፋሲል መዋኛ፣ ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ ራስ ግምብና ደረስጌ ማርያምን ይዟል ብለዋል፡፡
በዩኔስኮ 1979 ዓ.ም. በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የአፄ ፋሲለደስ ቤተ-መንግሥት፤ በውስጡ ያሉት ቤተ መንግሥቶች ከ100 በላይ ክፍሎች ያሏቸው ሲሆን፤ በአጠቃላይ 7 ሄክታር ወይንም 70 ሺሕ ስኩዌር ሜትር ይሸፍናል ሲሉ ገልጸዋል።
ቡድን መሪው አያይዘውም፤ ከጎንደር አብያተ መንግሥታት በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም ቅርሶች እየተጠገኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
“ጎንደር ከተማ በውስጧ ከሚገኙ ድንቅ ቅርሶቿ በተጨማሪ በጎንደር ዙሪያ ወረዳና አካባቢው በርካታ ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎች ጋር የተሳሰረች ከተማ ናት” ብለው፤ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እና ለውጭ ሀገር ቱሪስቶች መጥተው እንዲጎበኙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
