የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም. የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ሀይሉ፥ በቅድመ ምርጫ የተከናወኑ ስራዎችን እና በቀጣይ ቀናት የሚከናወኑ ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በእጩዎች ምዝገባ፣ በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ በእጩዎች አደራደር፣ በመራጮች ምዝገባ፣ በፓለቲካ ፓርቲዎች ነጻ የአየር ድልድልና ሌሎች በቅድመ ምርጫው የተከናወኑ ተግባራትን አብራርተዋል።
የመራጮች ምዝገባን በተመለከተ ምዝገባው በተሰጡት የምዝገባ ቀናት በስፋት መከናወኑንና በትምህርትና በሚሊተሪ ተቋማትም ጭምር መደረጉን ገልጸዋል።
የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎችም የምርጫ ምዝገባ መደረጉንም ጠቅሰው፥ ይሁንና በመራጮች ምዝገባ ሂደት በአንዳንድ አካባቢዎች አግባብ ያልሆኑ ሁኔታዎች በመኖራቸው ሙሉ ምዝገባው ተሰርዞ፥ መራጮች በምርጫ ቀን ተመዝግበው እንዲመርጡ መወሰኑን ገልጸዋል።
ቀጣይ ባሉት ቀናት ከማን ምን ይጠበቃል የሚለውን በተመለከተም ቦርዱ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን፣ ከግንቦት 20 ጀምሮ የጽሞና ግዜ እንደሚጀምርና የፓለቲካ ፓርቲዎች ባሉት ቀናት ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳቸውን እንዲያጠናቅቁ ቦርዱ ጥሪ አቅርቧል።
ከወሳኝ አገልግሎቶች ውጪ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚካሄድበት ቀን ዝግ እንደሚሆኑም የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ሀይሉ ተናግረዋል።
የምርጫ ቅስቀሳን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረግ የምርጫ ቅስቀሳ እንደማይፈቀድና ይህንን ቅስቀሳ ሲያደርግ የተገኘ የፓለቲካ ፓርቲ በህግ አግባብ እንደሚጠየቅም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
