የትምህርት ሚኒስቴር የ2018 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን “ሙሉ በሙሉ በበይነመረብ” ልፈትን ነው በማለቱ፣ መሰረተ ልማት ባልተሟላባቸው ት/ቤቶች ለሚፈተኑ ተማሪዎች ውጤት አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያመጣ በማሳሰብ ቋሚ ኮሚቴው መፍትሄ ጠየቀ።
ይህ የተባለው ሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት ሪፖርቱን፥ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የሚኒስቴሩ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እሸቱ ገላዬ፣ “የ2018 የ12 ዓ/ም ክፍል ፈተና 100% በበይነ መረብ (Online) ለመስጠት ከክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል” ብለዋል።
በ4 ሺህ 047 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች፣ የኢንተርናሽናል ት/ቤቶች የመፈተኛ ጣቢያን ጨምሮ በ15 ክልሎች፣ ከ148 ዞኖች፣ እንዲሁም ከ1 ሺህ 074 ወረዳዎች 503 ሺሕ 203 መደበኛ፣ 51 ሺሕ 762 የድጋሚ ተፈታኝ ተማሪዎች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
ይህ በእንዲሁ እያለ ፈተናው “ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ” ይሰጣል መባሉ ከወዲሁ ስጋት ገጥሞታል።
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ “የመሰረተ ልማት አቅርቦት የሌላቸው፤ መብራት ለወር፣ ለሁለት ሳምንት ተቋርጦ የሚቆይባቸው ወረዳዎች አሉ፤ ኔቶርክ የሚቆራረጥበት ሁኔታ አለ። አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል?” ሲሉ ትምህርት ሚኒስቴርን ጠይቀዋል።
“ባለን መረጃ መሰረት ትምህርት ሚኒስቴር ‘የ12ኛ ክፍል ፈተናን ሙሉ ለሙሉ በበይነ መረብ እሰጣለሁ’ ሲል ኮምፒዩተር ፍለጋ የሚሯሯጡ የትምህርት ተቋማት አሉ” ያሉት ነገሪ (ዶ/ር)፣ ከከተሞች በዘለለ በወረዳዎች ያለውን ሁኔታ ታይቶ እንደሆነም ጠይቀዋል።
በተያያዘ፣ የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ታደሰ ጌጡ፣ “የመብራት፣ የኮምፒዩተርና የኔትወርክ መሰረተ ልማት ባልተሟላባቸው ት/ቤቶች የሚፈተኑ ተማሪዎች ውጤት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ምን መፍትሄ ተቀምጧል?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፣ በምላሻቸው፣ “ምክር ቤቱ ያለው ፍርሃት እና ጭንቀት እኛም ጋር” አለ ብለው፣ የፈተናውን ክዋኔ በተመለከተ በየሳምንቱ የሚመሩት ብሔራዊ ቡድን መቋቋሙን በመግለጽ፣ ከቴሌ፣ መብራት ኃይል፣ ኢንሳ ጋር በመሆን በየዞኑ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ታደሰ ጌጡ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ደግሞ፣ “‘ከፍተኛ ተፅዕኖ’ ይኖረዋል የሚል እምነት የለንም” ሲሉ ገልጸው፣ “100% በበይነ መረብ እንፈትናለን ስንል ያለን ወደ 122 ሺሕ ኮምፒዩተሮችን ዝግጁ አድርገን ነው። በሁሉም ቦታ በተለያዩ አካባቢዎች መስጠት እንችላለን ብለን ነው” ብለዋል።
” በአንዳንድ ቦታዎች በእጃቸው ስልክ ያላቸው ፈተና መለማመድ ጀምረዋል። ኔትወርክ የሌለባቸው ቦታዎችን እስክናስተካክል ካልሆነ በቀር። እነርሱም ጋር ለወር፣ ሁለት ወር እንዲለማመዱ እናደርጋለን ” ነው ያሉት።
” ፈተናው ከመሰጠቱ በፊት ቢያንስ ከሁለት ወራት ጀምሮ የሙከራ ፈተና እንሰጣለን ” ሲሉ ተናግረው፣ ሁሉም ተማሪዎች ገብተው ከኮምፒዩተር ጋር ተለማምደው ነው የሚፈተኑት ብለዋል።
በበይነ መረብ ፈተና በሚሰጥበት ወቅት የመብራት መቆራረጥ በችግር የጠቀሱት የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ደግሞ፣ መሰረተ ልማት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ፈተናውን በ6 ዙር ለመስጠት መታቀዱን አመልክተዋል።
ኔትዎርክ በሌለበት አካባቢ ፈተና እንደማይሰጥና ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘም ከሚመለከተው ተቋም ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ የማይሳካ ከሆነ Backup plan አዘጋጅተን ነው እንጅ የምንገባው እኛ 100% እናደርጋለን በሚል ብቻ አይደለም ” ብለዋል።
@tikvahethiopia
