ዳሸን ባንክ በ”ሸሪክ” ከወለድ ነፃ አገልግሎቱ አማካኝነት ለኤሌጋንስ አስመጪና ላኪ ድርጅት የመጀመሪያውን ዙር 50 ዘመናዊ ቢ.ዋይ.ዲ. E2 (BYD E2) የኤሌክትሪክ መኪናዎች ግዢ ፋይናንስ በማድረግ አስረክቧል ፡፡
ኤሌጋንስ ተሽከርካሪዎቹን በኢትዮጵያ ለሜትር ታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚያውላቸው ሲሆን፣ የዳሸን ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ በዘርፉ የስራ ዕድሎችን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ባንኩ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት ባደረገው ጥረት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ “አስደናቂ” ዕድገት ማስመዝገቡን የዳሸን ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ቺፍ ኦፊሰር አቶ አምዱ አማን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እና ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማፍራት ችሏል ብለዋል፡፡
ባንኩ ከተሰበሰበው ሀብት ውስጥ ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከወለድ ነፃ በሆነ የፋይናንስ ሥርዓት ማቅረቡንም ጠቅሰዋል።
”ሸሪክ” አገልግሎት ስኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝቷል የተባለ ሲሆን፣ ባንኩ እ.ኤ.አ. በ2023 በባህሬን በተካሄደው 9ኛው የኢስላሚክ ሪቴል ባንክ ሽልማት ላይ “በኢትዮጵያ ጠንካራው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሰጪ” ተብሎ መሸለሙን አቶ አምዱ አስታውሰዋል፡፡
ርክክብ የተደረገባቸው 50 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የዳሸን ሸሪክ መለያ የተለጠፈባቸውና ባንኩን የሚያስተዋውቁ ሲሆን፣ የሜትር ታክሲ ተጠቃሚዎች የጉዞ ክፍያቸውን በዳሸን ሱፐር አፕ በኩል መክፈል ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
