በኢትዮጵያ የእስራኤል ባለልዩ መልዕክተኛና አምባሳደር ዶ/ር አብርሃም ንጉሤ አርብ መጋቢት 27 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት ይፋዊ መግለጫ፣ እስራኤል ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በመቀናጀት በኢራን ላይ የከፈተችው “ኦፕሬሽን ሮሪንግ ላይን” ሀገራቸው የህልውና አደጋን ለመቀልበስ የወሰደችው የግድ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ እንደገለጹት፣ የኢራኑ አያቶላህ አገዛዝ እስራኤልን ለማጥፋት ካለው ስትራቴጂ ባለመለወጡና የኑክሌር ፕሮግራሙን እንዲሁም የባሊስቲክ ሚሳኤል ማምረቻዎቹን ወደ መሬት ስር ምሽጎች በማዛወር “የማይደፈር” ለመሆን በመሞከሩ፣ እስራኤል አሁን እርምጃ የመውሰድ ወይም ነገ የማይቀለበስ አደጋ የመጋፈጥ ምርጫ ውስጥ ወድቃለች። በመሆኑም ይህ ዘመቻ የአገዛዙን የጥፋት አቅም ለማዳከም የታለመ እንጂ በምርጫ የመጣ ጦርነት እንዳልሆነ አብራርተዋል።
አምባሳደር አብርሃም በዝርዝር ባቀረቡት መግለጫ፣ የቴህራን አገዛዝ ሚሳኤሎች መካከለኛውን ምስራቅ አልፈው አውሮፓንና የአፍሪካ ቀንድን ጭምር ሊደርሱ እንደሚችሉ በመጠቆም፣ አገዛዙ በቅርቡ በአረብ ጎረቤቶቹ ላይ የፈጸመው ጥቃት የሰላማዊ ሰዎችን መኖሪያ፣ ሆቴሎችንና የኢነርጂ ተቋማትን ኢላማ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
እስራኤል በዚህ ዘመቻ ወቅት በአገዛዙ የጦር መሠረተ ልማቶች እና በኢራን ሕዝብ መካከል ግልጽ ልዩነት ማድረጓን ያረጋገጡት አምባሳደሩ፣ የኢራን ሕዝብ የራሱ አገዛዝ ሰለባ መሆኑንና ከሁለት ወራት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቹን በጭካኔ መግደሉን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ይህ ወታደራዊ እርምጃ የአገዛዙን የሽብር መረብ በመበጣጠስ፣ የኢራን ሕዝብ ነፃነቱን ዳግም የሚያገኝበትን ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ “ታሪክ ለአይሁድ ሕዝብ ያስተማረው ነገር ቢኖር ሊያጠፋን የሚዝትን አካል ችላ አለማለትን ነው” ያሉት አምባሳደሩ፣ በኑክሌር የታጠቀች ኢራን ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ስጋት እንደምትሆን አስገንዝበዋል።
ኦፕሬሽን ሮሪንግ ላይን የግዛት መስፋፋት ዘመቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊት እስራኤል ዜጎቿን ከጥፋት ለመታደግ የወሰደችው የመከላከያ እርምጃ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
አምባሳደር አብርሃም ንጉሤ አክለውም፣ እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሰላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ እያደረገች መሆኑንና የሽብር ምንጭ የሆነው አገዛዝ የጥፋት አጀንዳውን የሚያስፈጽምበት አቅም እንዳይኖረው በጽናት እንደምትቆም በኤምባሲው በኩል በወጣው መግለጫ አረጋግጠዋል።
