በ2016 በጀት ዓመትና ከዚያ በፊት ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከሕግ ውጭ የተፈጸሙ ክፍያዎች መሆናቸው በሒሳብ ምርመራ ተረጋግጦ፣ 21 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እና ከ23 ሺህ በላይ ዶላር (በአሁን ምንዛሬ 3.6 ሚሊዮን ብር) ለመንግሥት ተመላሽ እንዲሆን ጥፋቱን የፈጸሙ ተቋማት በደብዳቤ ተጠይቀው ነበር።
ይሁንና ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2017 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከተጠየቀው ገንዘብ ውስጥ ለመንግሥት ተመላሽ የተደረገው 31 በመቶው ወይም 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብሩ ብቻ ነው።
ያላግባብ ወጭ ተደርጓል፤ ለመንግስት ይመለስ የተባለው እና በውጭ ምንዛሬ 23,200 ዶላር መቶ በመቶ ለመንግስት ሳይመለስ ቀርቷል።
ተቋማቱ ሕግ ጥሰው ያላግባብ ወጪ ካደረጉት ውስጥ እስካሁን ለመንግሥት ያልመለሱትና ወደ 15 ቢሊዮን ብር የተጠጋ ገንዘብ በአስቸኳይ ተመላሽ እንዲያደርጉ በድጋሚ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።
ከህግ ውጭ የተከፈሉ እና ለመንግስት መመለስ አለባቸው የተባሉት በአብዛኛው ፦
– በጉምሩክ
– በገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች
– በዩኒቨርስቲዎች የተፈፀሙ ክፍያዎች መሆናቸው ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ከሕግ ውጭ ከወጣው ገንዘብ ውስጥ ከ32 እስከ 99 በመቶ የሚሆነውን ለመንግሥት ካዝና ተመላሽ ያደረጉ ተቋማት የሚከተሉት ናቸው፦
✅ የቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፦ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር
✅ የኮምቦልቻ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፦ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ
✅ የኤርፖርት ጉምሩክ ፦ 621 ሚሊዮን ብር
✅ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፦ 120.7 ሚሊዮን ብር
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ባክኖ እንዳይቀር እንዲህ ያለው የሒሳብ አያያዝ መዝረክረክ በአስቸኳይ እንዲታረምና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ በጥብቅ አስጠንቅቋል።
በሌላ በኩል ፥ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሒሳብ አያያዝ መመሪያዎችን በመጣስ ማስረጃ ሳይቀርብ፣ እንዲሁም መከፈል ካለበት በብልጫና በድጋሚ በተፈጸመ ክፍያ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ያለአግባብ ወጪ ማድረጋቸው ተረጋግጧል።
የዋና ኦዲተር በሪፖርቱ ይፋ ያደረጋቸው ተጨማሪ ግኝቶች የሚከተሉት ናቸው።
• የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገበ ➔ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ
በብልጫና በድጋሚ ያላግባብ የተፈጸመ ክፍያ ➔ 280.6 ሚሊዮን ብር
• ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ወጪ ➔
57.8 ሚሊዮን ብር
• ማስረጃ ሳይቀርብ ወጪ የተደረገ ➔ 35.8 ሚሊዮን ብር
በብልጫና በድጋሚ ያላግባብ ክፍያ የፈጸሙ ተቋማትእነማን ናቸው
?
– የጤና ሚኒስቴር ➔ 231.1 ሚሊዮን ብር
– የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ➔ 23 ሚሊዮን ብር
– የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ➔ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ
– የቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ➔ 2.4 ሚሊዮን ብር
– ጅማ ዩኒቨርሲቲ ➔ 2.1 ሚሊዮን ብር
የተሟላ የወጪ ማስረጃ ካልቀረበበት 1.1 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት ፦
° የሞያሌ ጉምሩክ ➔ 25.4 ሚሊዮን ብር
° የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ➔ 23.4 ሚሊዮን ብር
° የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ➔ 7.5 ሚሊዮን ብር
° የማዕድን ልማት ኢንስቲትዩት ➔ 6.6 ሚሊዮን ብር
° የማዕድን ሚኒስቴር ➔ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ
° የባህር ዳር ጉምሩክ ➔ 4.7 ሚሊዮን ብር
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያለበቂ ማስረጃ ክፍያ መፈጸምን ጨምሮ ደንብና መመሪያ ተጥሰው የሚፈጸሙ ክፍያዎች ተጠያቂነትን እንደሚያስከትሉ በመግለጽ፣ ገንዘቡ በአስቸኳይ ተመላሽ እንዲደረግና እንዲህ ያለው መዝረክረክ እንዲታረም በጥብቅ አስጠንቅቋል።
የሸገር ኤፍ ኤም 102.1
