የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የስድስት ወር የስራ አፈፃፀሙን አስመልክቶ ለብዙሃን መገናኛ መግለጫ ሰጥቷል።
ባለፉት ስድስት ወራት በማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ መሻሻል መኖሩን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮምሽነር አቶ ብርሀኑ አዴሎ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ከፌደራል እና ከክልል መንግስታት ጋር ባደረገዉ ዉይይቶች 1ሺ 136 የህግ ታራሚዎች ጉዳያቸው ተገምግሞ በዋስ እንዲፈቱ ማድረግ ተችሏል ሲል አስታውቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ 119ኙን ለማስፈታት ሙከራ ተደርጎ ተጠርጥረው የተያዙበት ምክንያት በዋስ እንዲፈቱ ለማድረግ አስቻይ ባለመሆኑ፤የፍርድ ቀጠሯቸውን እንዲከታተሉ መወሰኑ ተገልፃል።
በማረሚያ ቤት የእለት ምግብ ፍጆታ ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲነሳ ቢቆይም በተወሰነ መንገድ በአንዳንድ የማረሚያ ቤቶች ችግሩን ለመቅረፍ መሞከሩን ቢገልፁም ፤ ነገር ግን አሁንም ብዙ ቀሪ ስራዎች መኖራቸዉን ጠቁመዋል።
ሌሎች ታራሚዎች የሰብዓዊ የመብት ጥሰት እንዳይፈፀምባቸው እና ጫና እንዳይደርስባቸዉ ክትትል እየተደረገ መሆኑን በተሰጠው መግለጫ ተመላክቷል።
